ኤርምያስ 1:5-17
ኤርምያስ 1:5-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።” እኔም፥ “ወዮልኝ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ ሕፃን ነኝና እናገር ዘንድ አልችልም” አልሁ። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፥ “ወደምልክህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና፦ ሕፃን ነኝ አትበል። እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋራ ነኝና ከፊታቸው የተነሣ አትፍራ” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም አለኝ፥ “እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤ እነሆ ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾሜሃለሁ።” ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል፥ “ኤርምያስ ሆይ! ምን ታያለህ?” እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም፥ “የሎሚ በትር አያለሁ” አልሁ። እግዚአብሔርም፥ “የተናገርሁትን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና መልካም አይተሃል” አለኝ። ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ምን ታያለህ?” እኔም፥ “የሚፈላ አፍላል አያለሁ፤ ፊቱም ወደ ሰሜን ወገን ነው” አልሁ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ከሰሜን ወገን ክፉ ነገር በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ ይፈስሳል። እነሆ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታቱን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋና በቅጥርዋ ሁሉ ላይ፥ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተዉ፥ ለሌሎችም አማልክት ስለ ሠዉ፥ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፤ ተነሥም፤ ያዘዝሁህንም ሁሉ ንገራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትፍራ። በፊታቸውም አትደንግጥ አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ይላል እግዚአብሔር።
ኤርምያስ 1:5-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“በማሕፀን ሳልሠራህ ዐወቅሁህ፤ ከመወለድህ በፊት ለየሁህ፤ ለሕዝቦችም ነቢይ እንድትሆን ሾምሁህ።” እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” አልሁ። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ “ ‘ገና ሕፃን ልጅ ነኝ’ አትበል፤ ወደምልክህ ሁሉ ሄደህ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ትናገራለህ፤ እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራቸው” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰና እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ቃሌን በአፍህ አኑሬአለሁ፤ እንግዲህ፣ እንድትነቅልና እንድታፈርስ፣ እንድታጠፋና እንድትገለብጥ፣ እንድታንጽና እንድትተክል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾምሁህ።” የእግዚአብሔር ቃል፣ “ኤርምያስ ሆይ፣ ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም፣ “የአልሙን በትር አያለሁ” አልሁ። እግዚአብሔርም፣ “ትክክል አይተሃል፤ ቃሌን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና” አለኝ። ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቃል፣ “ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም፣ “አንድ የሚፈላ ማሰሮ አያለሁ፤ አፉም ከሰሜን ወደዚህ ያዘነበለ ነው” አልሁ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ከሰሜን በምድሪቱ በሚኖሩ ሁሉ ላይ ድንገት መዓት ይወርድባቸዋል። እነሆ፤ የሰሜን መንግሥታትን ሕዝቦች ሁሉ እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ንጉሦቻቸው ይመጣሉ፤ ዙፋናቸውን በኢየሩሳሌም መግቢያ በሮች፣ በቅጥሮቿ ዙሪያ ሁሉ፣ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ይዘረጋሉ። እኔን በመተው ክፋት ስለ ሠሩ፣ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው የሠሯቸውን ስላመለኩ፣ በሕዝቤ ላይ ፍርድን ዐውጄአለሁ። “አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፤ ተነሥተህም ያዘዝሁን ሁሉ ንገራቸው፤ አትፍራቸውም፤ አለዚያ በፊታቸው አስፈራሃለሁ።
ኤርምያስ 1:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ። እኔም፦ ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም አልሁ። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፦ ወደምሰድድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና፦ ብላቴና ነኝ አትበል። እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና ከፊታቸው አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም፦ እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፥ እነሆ፥ ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ አድርጌሃለሁ አለኝ። ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል፦ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም፦ የለውዝ በትር አያለሁ አልሁ። እግዚአብሔርም፦ እፈጽመው ዘንድ በቃሌ እተጋለሁና መልካም አይተሃል አለኝ። ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል፦ ምን ታያለህ? እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም፦ የሚፈላ አፍላል አያለሁ፥ ፊቱም ከሰሜን ወገን ነው አልሁ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ከሰሜን ወገን ክፉ ነገር በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ ይገለጣል። እነሆ፥ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋ በቅጥርዋ ሁሉ ላይ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተዉ ለሌሎችም አማልክት ስላጠኑ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፥ ተነሥም፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ንገራቸው፥ በፊታቸው እንዳላስፈራህ አትፍራቸው።
ኤርምያስ 1:5-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ኤርምያስ ሆይ! ገና በእናትህ ማሕፀን እንድትፀነስ ከማድረጌ በፊት ዐውቄሃለሁ፤ ከመወለድህም በፊት አንተን በመለየት ለሕዝቦች ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ።” እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ገና ልጅ ስለ ሆንኩ እንዴት እንደምናገር አላውቅም” ብዬ መለስኩለት። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፦ “ ‘ገና ልጅ ነኝ’ አትበል፤ የምትሄደው እኔ ወደምልክህ ቦታ ነው፤ የምትናገረውም እኔ የማዝህን ሁሉ ነው፤ እኔ ከአንተ ጋር ሆኜ ስለምታደግህ እነርሱን ከቶ አትፍራቸው፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ!” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እጁን ዘርግቶ ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እንዲህም አለኝ፦ “እነሆ የምትናገረውን ቃሌን ሰጥቼሃለሁ፤ እነሆ መንቀልና ማፍረስ፥ ማጥፋትና መገለባበጥ፥ ማነጽና መትከል እንድትችል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ።” እግዚአብሔርም “ኤርምያስ ሆይ! የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም “የለውዝ ቅርንጫፍ አያለሁ” አልኩት። እግዚአብሔርም “በትክክል አይተሃል፤ እኔም እንዲሁ ቃሌ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን አተኵሬ እመለከታለሁ” አለኝ። እንደገናም እግዚአብሔር “ሌላስ የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም “በስተ ሰሜን በኩል አንድ ማሰሮ ሲፈላ አያለሁ፤ ወደዚህም ለመገልበጥ አዘንብሎአል” ስል መለስኩለት። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “በስተ ሰሜን በኩል ጥፋት ገንፍሎ በዚህች ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይከነበልባቸዋል፤ በስተ ሰሜን የሚኖሩ ሕዝቦች ወደዚህ እንዲመጡ እጠራለሁ፤ ኢየሩሳሌምንና በዙሪያዋ ያሉትን የይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ይይዙአቸዋል፤ ከዚያም በኢየሩሳሌም መግቢያ በር ላይ ዙፋናቸውን ይዘረጋሉ። ሕዝቤ ኃጢአት ስለ ሠሩ እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ እኔን ትተው ለሌሎች አማልክት ዕጣን ያጥናሉ፤ ምስሎችንም ሠርተው ይሰግዱላቸዋል። ስለዚህ ኤርምያስ ሆይ! እኔ የማዝህን ሁሉ እንድትነግራቸው ወደ እነርሱ ለመሄድ ተዘጋጅ፤ እነሆ እነርሱን አትፍራ፤ አለበለዚያ በእነርሱ ፊት የበለጠ እንድትፈራ አደርግሃለሁ።
ኤርምያስ 1:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“በማሕፀን ውስጥ ሳልሠራህ በፊት አውቄሃለሁ፥ ከማሕፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ።” እኔም፦ “ወዮ! ጌታ አምላኬ፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እንዴት እንደምናገር አላውቅም” አልሁ። ጌታ ግን እንዲህ አለኝ፦ “ ‘ብላቴና ነኝ’ አትበል፤ ወደ ምልክህ ሁሉ ትሄዳለህ፥ የማዝህንም ሁሉ ትናገራለህ። እኔ ላድንህ ከአንተ ጋር ነኝና በእነርሱ ምክንያት አትፍራ፥ ይላል ጌታ።” ጌታም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እንዲህም አለኝ፦ “እነሆ፥ ቃሎቼን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤ እነሆ፥ ዛሬ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ እንድትነቅልና እንድታፈርስ፥ እንድታጠፋና እንድትገለባብጥ፥ እንድታንጽና እንድትተክል ሾሜሃለሁ።” ደግሞ የጌታ ቃል፦ “ኤርምያስ ሆይ! ምን ታያለህ?” እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም “የለውዝ በትር አያለሁ” አልኩት። ጌታም “ቃሌን ልፈጽመው ነቅቼ እየጠበቅሁ ነኝና መልካም አይተሃል” አለኝ። ሁለተኛም ጊዜ የጌታ ቃል “ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም “የሚፈላ የሸክላ ድስት ከሰሜን ፊቱን አዘንብሎ አያለሁ” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለኝ “ከሰሜን በኩል የሚነሣ ጥፋት በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ በድንገት ይመጣባቸዋል። እነሆ፥ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋም ባለ ቅጥርዋ ሁሉ ላይ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ፥ እኔን ትተውኛል፤ ለሌሎችም አማልክት ዕጣንን አጥነዋል፤ ለእጃቸውም ሥራዎች ሰግደዋልና። አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፥ ተነሥም፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ንገራቸው፤ በእነርሱ ፊት እንዳላስፈራህ አትፍራቸው።