የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 1

1
1በብንያም አገር በዓናቶት ከነበሩ ካህናት የሆነ የኬልቅያስ ልጅ የኤርምያስ ቃላት። 2#2ነገ. 22፥3—23፥27፤ 2ዜ.መ. 34፥8—35፥19።በይሁዳ ንጉሥ በአሞን#1፥2 አንዳንድ ትርጉሞች አሞጽ ይላሉ። ልጅ በኢዮስያስ ዘመን፥ በመንግሥቱ በዓሥራ ሦስተኛው ዓመት የጌታ ቃል ወደ እርሱ መጣ። 3#2ነገ. 23፥36—24፥7፤ 2ዜ.መ. 36፥5-8፤ 2ነገ. 24፥18—25፥21፤ 2ዜ.መ. 36፥11-21።በይሁዳም ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን፥ እስከ ይሁዳ ንጉሥ እስከ ኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ ዐሥራ አንደኛው ዓመት ፍጻሜ፥ ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት እስከ አምስተኛው ወር ድረስ መጣ።
የነቢዩ ኤርምያስ ጥሪና ተልእኮ
4የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5“በማሕፀን ውስጥ ሳልሠራህ በፊት አውቄሃለሁ፥ ከማሕፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ።” 6እኔም፦ “ወዮ! ጌታ አምላኬ፥ እነሆ፥ ብላቴና ነኝና እንዴት እንደምናገር አላውቅም” አልሁ። 7ጌታ ግን እንዲህ አለኝ፦ “ ‘ብላቴና ነኝ’ አትበል፤ ወደ ምልክህ ሁሉ ትሄዳለህ፥ የማዝህንም ሁሉ ትናገራለህ። 8እኔ ላድንህ ከአንተ ጋር ነኝና በእነርሱ ምክንያት አትፍራ፥ ይላል ጌታ።” 9ጌታም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እንዲህም አለኝ፦ “እነሆ፥ ቃሎቼን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤ 10እነሆ፥ ዛሬ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ እንድትነቅልና እንድታፈርስ፥ እንድታጠፋና እንድትገለባብጥ፥ እንድታንጽና እንድትተክል ሾሜሃለሁ።”
11ደግሞ የጌታ ቃል፦ “ኤርምያስ ሆይ! ምን ታያለህ?” እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም “የለውዝ በትር አያለሁ” አልኩት። 12ጌታም “ቃሌን ልፈጽመው ነቅቼ እየጠበቅሁ ነኝና መልካም አይተሃል” አለኝ።
13ሁለተኛም ጊዜ የጌታ ቃል “ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም “የሚፈላ የሸክላ ድስት ከሰሜን ፊቱን አዘንብሎ አያለሁ” አልሁ። 14ጌታም እንዲህ አለኝ “ከሰሜን በኩል የሚነሣ ጥፋት በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ በድንገት ይመጣባቸዋል። 15እነሆ፥ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታትን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋም ባለ ቅጥርዋ ሁሉ ላይ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። 16ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ፥ እኔን ትተውኛል፤ ለሌሎችም አማልክት ዕጣንን አጥነዋል፤ ለእጃቸውም ሥራዎች ሰግደዋልና። 17አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፥ ተነሥም፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ንገራቸው፤ በእነርሱ ፊት እንዳላስፈራህ አትፍራቸው። 18እነሆ እኔም፥ በምድሪቱ ሁሉ ላይ በይሁዳም ነገሥታት በአለቆችዋና በካህናትዋ ላይ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ የተመሸገ ከተማ፥ የብረትም ዓምድ፥ የናስም ቅጥሮች ዛሬ አድርጌሃለሁ። 19ከአንተም ጋር ይዋጋሉ፥ ነገር ግን አንተን ላድንህ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፥ ይላል ጌታ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ