የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ መግቢያ

መግቢያ
የኬልቅያስ ልጅ ኤርምያስ የካህናት ወገን ከሆነ ቤተሰብ፤ በቢንያም ግዛት በምትገኝ በዓናቶት በምትባል በአነስተኛ ከተማ ተወለደ። ኤርምያስ የነቢይነቱን አገልግሎት የጀመረው በኢዮስያስ በነገሠ በዓሥራ ሦስተኛው ዓመት 627 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። አገልግሎቱንም ያበቃው ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በ 587 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከደመሰስዋት በኋላ ነበር። ነቢዩ ኤርምያስ ራሱን ከሕዝቡ መራራ መከራ ጋር አንድ ስላደረገ ትዳር ሳይመሠርት ቀረ (16፥1-4)። ትንቢተ ኤርምያስ የመጽሐፍ ቅዱስ ረጅሙ መጽሐፍ ነው። ነቢዩ ኤርምያስ ከአሦር አገዛዝ በከፊል ነጻነት ባገኘው በኢዮስያስ፤ የግብጽ ገባር በነበረው በኢዮአቄም፤ በባቢሎን አገዛዝ ሥር በነበረው በሴዴቅያስ ከዚያም ለባቢሎን እንደ ተቀጽላ አስተዳዳሪ በነበረው ጎዶልያስ ዘመነ መንግሥት ሥር አገልግሎአል። መጽሐፉ ምድሪቱ በጣዖት እንደተሞላች (2፥4-13፤፤ 5፥20-25 28፥13-17) በውጤቱም አስከፊ የእግዚአብሔር ቊጣና ፍርድ እንደሚመጣባት በዋነኝነት የሚናገር ነው። ሕዝቡ እውነተኛ ንስሐ የሚገባ ቢሆን ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ የመዳን ተስፋ እንደሚኖረው ይገልጻል (3፥9—4፥2)።
ነቢዩ ኤርምያስ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ቤተ መቅደስ እንዳይገባ ተከልክሎአል (15፥10)፤ አድሎ ተደርጐበታል (36፥5)፤ ተረግሞአል (17፥15)፤ ሤራ ተሢሮበታል (18፥18፤ 20፥10)፤ በውኃ ማጠራቀምያ ጕድጓድ ተጥሎአል (38፥5)። ይህም ሁኔታ የነቢዩ ኤርምያስ ኑዛዜ ተብለው በሚታወቁት ምዕራፎች (11፥18—12፥6፤ 15፥10-21፤ 17፥14-18፤ 18፥18-23፤ 20፥7-18) ውስጥ ተዘርዝሯል። በዚህም የተነሣ ነቢይ መሆን እንደቆጨው (17፥14-18)፤ እግዚአብሔርም እንዳስቀየመው (15፥15-18)፤ የተወለደበትን ቀን እንደረገመና ሞትንም እንደተመኘ (20፥14-18) ተናግሮአል። በሌላ በኩል፥ ምንም መከራ ቢበዛበትም ነቢዩ ኤርምያስ እግዚአብሔርን ያወድስ ነበር። እንዲሁም ለሕዝቡ በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት መማለድን አልተወም ነበር (15፥10፤ 18፥20፤ 7፥16)። ከዚህም በኋላ በባቢሎን ላይ ለማመፅ ኤዶም፤ ሞዓብ፤ አሞን፤ ጢሮስና ሲዶና በኢየሩሳሌም መሰብሰባቸውንና (27፥3) በእነዚህም መንግሥታት ላይ ጌታ ፍርዱን እንደሚያመጣ ነቢዩ ይገልጻል። ነቢዩ ኤርምያስ እግዚአብሔር ባቢሎንን እንደሾማት ፍርዱንም የሚፈጽምባት መሣርያ እንደ ሆነች ተናግሮአል (4-6)። ይህም ትንቢት ሕዝቡ ንስሐ ባለመግባቱና በኃጢአቱ በመጽናቱ (13፥23) ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በደመሰስዋት ጊዜ ተፈጽሟል። በመጨረሻም በምድሪቱ የነበሩት ትሩፋን ጎዶልያስን ከገደሉ በኋላ ነቢዩ ኤርምያስንና ጸሐፊውን ባሮክን በመያዝ ወደ ግብጽ መሸሻቸውን ይገልጻል (43፥6-7)።
ትንቢተ ኤርምያስ በግጥምና በዝርው ተጽፎአል። ልብን በብርሃን የሚሞላ የተስፋ ቃል ኪዳን ይገኝበታል። መጽሐፉ በዋነኝነት ስለ ጌታ የፍርድ መልእክት ይናገራል። ይህም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከአደጋ ለማዳን ያለመ ነው። ትንቢተ ኤርምያስ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ውስጣዊና ግላዊ ዝምድና ሊኖረው እንደሚገባው፤ ውጫዊ ሥርዓተ አምልኮ ለብቻው ፍሬ እንደሌለው ያስረዳል (6፥16-21፤ 7፥21-23)። እውነተኛ ንስሐና ከልብ የመነጨ ተአዝዞ እንደሚገባ፤ ውስጣችንንም በፍጹም ማጽዳትና መለወጥ እንዳለብን ያስተምራል (4፥3-4)። በዚህም አካሄድ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰሙና የሚቀበሉ ተስፋ የሌላቸው አለመሆናቸውን በመልእክቱ ይናገራል። ነቢዩ በመከራ የተጐሳቈለውን ሕዝቡን ያለ ተስፋና ያለ መጽናናት አልተወውም። የነቢዩ ኤርምያስ ተልእኮ ለማፍረስና ለመንቀል ብቻ ሳይሆን ለማነጽና ለመትከልም ነውና (18፥7-9)። ይህንንም የተስፋ ቃል ለማጽናት ነቢዩ ለሕዘቡ “ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል” በማለት የእግዚአብሔርን አዲሱን ቃል ኪዳን ያበሥራል (30፥31-34)።
የመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘት
በኢዮስያስ ዘመን የተነገረ ትንቢት (1፥1—6፥30)
በኢዮአቄም ዘመን ቀደም ብሎ የተነገረ ትንቢት (7፥1—20፥18)
በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረ ትንቢት (21፥1—25፥38)
የቤተ መቅደሱ ስብከት (26፥1-24)
ከሐሰተኛ ነብያት ጋር የተደረገ ክርክር (27፥1—29፥32)
ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ይሁዳ መታደስ የተነገረ ትንቢት (30፥1—35፥19)
ኤርምያስ እና የኢየሩሳሌም ውድቀት (36፥1—45፥5)
በተለያዩ አገሮች መንግሥታት ላይ የተነገረ የፍርድ ትንቢቶች (46፥1—51፥64)
ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ (52፥1-34)
ምዕራፍ

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ