የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኤርምያስ 1:5-17

ኤርምያስ 1:5-17 NASV

“በማሕፀን ሳልሠራህ ዐወቅሁህ፤ ከመወለድህ በፊት ለየሁህ፤ ለሕዝቦችም ነቢይ እንድትሆን ሾምሁህ።” እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” አልሁ። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ “ ‘ገና ሕፃን ልጅ ነኝ’ አትበል፤ ወደምልክህ ሁሉ ሄደህ፣ ያዘዝሁህን ሁሉ ትናገራለህ፤ እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራቸው” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰና እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ቃሌን በአፍህ አኑሬአለሁ፤ እንግዲህ፣ እንድትነቅልና እንድታፈርስ፣ እንድታጠፋና እንድትገለብጥ፣ እንድታንጽና እንድትተክል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾምሁህ።” የእግዚአብሔር ቃል፣ “ኤርምያስ ሆይ፣ ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም፣ “የአልሙን በትር አያለሁ” አልሁ። እግዚአብሔርም፣ “ትክክል አይተሃል፤ ቃሌን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና” አለኝ። ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቃል፣ “ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም፣ “አንድ የሚፈላ ማሰሮ አያለሁ፤ አፉም ከሰሜን ወደዚህ ያዘነበለ ነው” አልሁ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ከሰሜን በምድሪቱ በሚኖሩ ሁሉ ላይ ድንገት መዓት ይወርድባቸዋል። እነሆ፤ የሰሜን መንግሥታትን ሕዝቦች ሁሉ እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ንጉሦቻቸው ይመጣሉ፤ ዙፋናቸውን በኢየሩሳሌም መግቢያ በሮች፣ በቅጥሮቿ ዙሪያ ሁሉ፣ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ይዘረጋሉ። እኔን በመተው ክፋት ስለ ሠሩ፣ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው የሠሯቸውን ስላመለኩ፣ በሕዝቤ ላይ ፍርድን ዐውጄአለሁ። “አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፤ ተነሥተህም ያዘዝሁን ሁሉ ንገራቸው፤ አትፍራቸውም፤ አለዚያ በፊታቸው አስፈራሃለሁ።