የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 1:5-17

ትንቢተ ኤርምያስ 1:5-17 አማ05

“ኤርምያስ ሆይ! ገና በእናትህ ማሕፀን እንድትፀነስ ከማድረጌ በፊት ዐውቄሃለሁ፤ ከመወለድህም በፊት አንተን በመለየት ለሕዝቦች ነቢይ አድርጌ ሾሜሃለሁ።” እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ገና ልጅ ስለ ሆንኩ እንዴት እንደምናገር አላውቅም” ብዬ መለስኩለት። እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፦ “ ‘ገና ልጅ ነኝ’ አትበል፤ የምትሄደው እኔ ወደምልክህ ቦታ ነው፤ የምትናገረውም እኔ የማዝህን ሁሉ ነው፤ እኔ ከአንተ ጋር ሆኜ ስለምታደግህ እነርሱን ከቶ አትፍራቸው፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ!” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እጁን ዘርግቶ ከንፈሮቼን ዳሰሰ፤ እንዲህም አለኝ፦ “እነሆ የምትናገረውን ቃሌን ሰጥቼሃለሁ፤ እነሆ መንቀልና ማፍረስ፥ ማጥፋትና መገለባበጥ፥ ማነጽና መትከል እንድትችል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ።” እግዚአብሔርም “ኤርምያስ ሆይ! የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም “የለውዝ ቅርንጫፍ አያለሁ” አልኩት። እግዚአብሔርም “በትክክል አይተሃል፤ እኔም እንዲሁ ቃሌ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን አተኵሬ እመለከታለሁ” አለኝ። እንደገናም እግዚአብሔር “ሌላስ የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም “በስተ ሰሜን በኩል አንድ ማሰሮ ሲፈላ አያለሁ፤ ወደዚህም ለመገልበጥ አዘንብሎአል” ስል መለስኩለት። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “በስተ ሰሜን በኩል ጥፋት ገንፍሎ በዚህች ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይከነበልባቸዋል፤ በስተ ሰሜን የሚኖሩ ሕዝቦች ወደዚህ እንዲመጡ እጠራለሁ፤ ኢየሩሳሌምንና በዙሪያዋ ያሉትን የይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ይይዙአቸዋል፤ ከዚያም በኢየሩሳሌም መግቢያ በር ላይ ዙፋናቸውን ይዘረጋሉ። ሕዝቤ ኃጢአት ስለ ሠሩ እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ እኔን ትተው ለሌሎች አማልክት ዕጣን ያጥናሉ፤ ምስሎችንም ሠርተው ይሰግዱላቸዋል። ስለዚህ ኤርምያስ ሆይ! እኔ የማዝህን ሁሉ እንድትነግራቸው ወደ እነርሱ ለመሄድ ተዘጋጅ፤ እነሆ እነርሱን አትፍራ፤ አለበለዚያ በእነርሱ ፊት የበለጠ እንድትፈራ አደርግሃለሁ።