ኢሳይያስ 7:1-25
ኢሳይያስ 7:1-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የአራም ንጉሥ ረአሶን፥ የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ሊይዙአትም አልቻሉም። ለዳዊት ቤትም፥ “አራም ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል” የሚል ወሬ ተነገረ፤ የእርሱም ልብ የሕዝቡም ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ ተናወጠ። እግዚአብሔርም ኢሳይያስን አለው፥ “አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው መታጠቢያ ቦታ ውጡ፤ እንዲህም በለው፥ “ተጠበቅ፥ ዝምም በል፤ አትፍራ፤ ከእነዚህ ከሚጤሱ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፥ የተነሣ ልብህ አይደንግጥ፤ ከተቈጣሁ በኋላ ይቅር እላለሁና። የአራም ልጅና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ፦ ክፉ ምክርን ተማከሩብህ እንዲህ ብለው፦ ወደ ይሁዳ እንውጣና እንነጋገራቸው፤ ወደ እኛም እንመልሳቸው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባቸው፤” የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም። የአራም ራስ ደማስቆ ነው፤ የደማስቆም ራስ ረአሶን ነው፤ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ የኤፍሬም መንግሥት ከሕዝብ ይጠፋል፤ የኤፍሬምም ራስ ሳምሮን ነው፤ የሳምሮንም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ነው። ባታምኑ አትጸኑም።” እግዚአብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለአንተ ለምን።” አካዝም፥ “አልለምንም፤ አምላኬ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ። እርሱም አለ፥ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፤ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? እግዚአብሔርን ታደክማላችሁ፤ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሳያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት፥ መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ፥ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ሀገር ባድማ ትሆናለች። እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው።” በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በግብፅ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝንብ፥ በአሦርም ሀገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል። ይመጡማል፤ እነርሱም ሁሉ በሸለቆ፥ በመንደሮች፥ በምድር ጕድጓድ፥ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በጫካ ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ። በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ ባመጣው ታላቅ ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፤ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይላጫል። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሰው ከላሞቹ አንዲት ጊደርንና ሁለት በጎችን ያሳድጋል፤ የአንዲት በግ ወተትም ሁለት ሰዎችን ያጠግባል። ወተትም ይበዛል፤ በሀገሪቱ መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል። በዚያም ወራት እንዲህ ይሆናል፤ ወይን በሀገሩ ሁሉ የበጀ ይሆናል፤ የአንድ ሺህ የወይን ዳስ ዋጋ አንድ ሺህ የብር ሰቅል ይሆናል። ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ምድር ሁሉ ትጠፋለች፤ እሾህንና ኵርንችትንም ትሞላለች፤ ፍርሀትም ይመጣል። በፍላጻና በቀስት ይገቡባታል፤ ምድሪቱ ሁሉ ትጠፋለችና፥ እሾህንና ኵርንችትንም ትሞላለችና። በሚታረሰውም ተራራ ሁሉ ላይ ፍርሀት ይመጣል፤ የበጎች መሰማርያ ይሆናል፤ በሬዎችም ይረግጡታል፤ እሾህና ኵርንችትም ያጠፋዋል።
ኢሳይያስ 7:1-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የዖዝያን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፣ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም። ለዳዊት ቤት፣ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፣ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ። እግዚአብሔርም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “አንተና ልጅህ ሸአር ያሹብ አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤ እንዲህም በለው፤ ‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ፤ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጕማጆች፣ በሶርያና በንጉሥዋ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቍጣ አትሸበር። ሶርያ ኤፍሬምና፣ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤ “ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው፤ ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባት።” ጌታ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤ ከቶም አይደረግም፤ የሶርያ ራስ ደማስቆ፣ የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ፣ የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም ይቀራል። የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፣ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፣ ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ ” እንደ ገናም እግዚአብሔር አካዝን እንዲህ አለው፤ “ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከእግዚአብሔር ከአምላክህ ለምን።” አካዝ ግን፣ “አልለምንም፣ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ። ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ፤ የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው።” በዚያን ቀን እግዚአብሔር ራቅ ካሉት ከግብፅ ወንዞች ዝንቦችን፣ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። እነርሱም በሙሉ መጥተው፣ በየበረሓው ሸለቆ፣ በየዐለቱ ንቃቃት፣ በየእሾኹ ቍጥቋጦና በየውሃው ጕድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። በዚያን ቀን፣ እግዚአብሔር ከወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ፣ ማለትም በአሦር ንጉሥ፣ የራስና የእግር ጠጕራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። በዚያን ቀን፣ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። በዚያን ቀን ሺሕ ሰቅል ብር የሚያወጣ አንድ ሺሕ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፣ ኵርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። ምድሪቱ በኵርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፣ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ ኵርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደ ነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብታዎች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።
ኢሳይያስ 7:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ሆነ፥ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፥ ሊያሸንፉአትም አልቻሉም። ለዳዊትም ቤት፦ ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል የሚል ወሬ ተነገረ፥ የእርሱም ልብ የሕዝቡ ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ። እግዚአብሔርም ኢሳይያስን አለው፦ አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፥ እንዲህም በለው፦ ተጠበቅ፥ ዝምም በል፥ ስለ እነዚህ ስለሚጤሱ ስለ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፥ ስለ ሶርያና ስለ ረአሶን ስለ ሮሜልዩም ልጅ ቍጣ አትፍራ፥ ልብህም አይድከም። ሶርያና ኤፍሬም የሮሜልዩም ልጅ፦ ወደ ይሁዳ እንውጣ እናስጨንቀውም፥ እንስበረውም፥ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት ብለው ክፋት ስለ መከሩብህ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም። የሶርያ ራስ ደማስቆ ነው፥ የደማስቆም ራስ ረአሶን ነው፥ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራልና ሕዝብ አይሆንም፥ የኤፍሬምም ራስ ሰማርያ ነው፥ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። ባታምኑ አትጸኑም። እግዚእብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለምን። አካዝም፦ አልለምንም፥ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም አለ። እርሱም አለ፦ እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፥ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፥ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፥ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። ሕፃኑም ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች። እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፥ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ እግዚአብሔር በግብፅ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝምብ በአሦርም አገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል። ይመጡማል፥ እነርሱም ሁሉ በበረሐ ሸለቆ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በእሾህ ቍጥቋጦ ሁሉ ላይ በማሰማርያውም ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ። በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፥ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይበላል። በዚያን ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ሰው አንዲት ጊደርን ሁለት በጎችንም ያሳድጋል፥ ከሚሠጡት ወተት ብዛት የተነሣ ቅቤ ይበላል፥ በአገሪቱም መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ሺህ ብር የተገመተ ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ሥፍራ ሁሉ ለኵርንችትና ለእሾህ ይሆናል። ኵርንችትና እሾህ በምድር ሁሉ ላይ ነውና በፍላጻና በቀስት ወደዚያ ይገባሉ። በመቈፈርያም ወደ ተቈፈሩ ኮረብቶች ሁሉ ከኵርንችትና እሾህ ፍርሃት የተንሣ ወደዚያ አትሄድም፥ ነገር ግን የበሬ ማሰማርያና የበግ መራገጫ ይሆናል።
ኢሳይያስ 7:1-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዖዝያን ልጅ ከኢዮአታም የተወለደው አካዝ በይሁዳ በነገሠበት ዘመን፥ የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ የረማልያ ልጅ ፋቁሔ ጦርነት ማስነሣት ፈልገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ነገር ግን ኢየሩሳሌምን ድል ሊያደርጉአት አልቻሉም። ሶርያ ከእስራኤል መንግሥት ጋር በመተባበር የጦር ቃል ኪዳን መግባትዋን የይሁዳ ንጉሥ በሰማ ጊዜ እርሱና ሕዝቡ ደንግጠው ልባቸው በነፋስ እንደ ተመታ ዛፍ ተናወጠ። እግዚአብሔርም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፦ “አንተና ልጅህ ሼርያሹብ ንጉሥ አካዝን ለመገናኘት ውጡ፤ እርሱንም ከላይኛው ኩሬ ውሃ በሚመጣበት በልብስ አጣቢዎች ቦታ ታገኙታላችሁ። ረጋ እንዲል፤ እንዳይፈራ፥ በእሳት ተቀጣጥሎ እንደሚነድ እንደ ግንድ ጢስ በሆኑት በሬዚንና በሶርያው በሬማልያ ልጅ ምክንያት እንዳይሸበር ንገረው። በእርግጥ ሶርያውያን ከእስራኤላውያንና ከንጉሣቸው ጋር ግብረ አበር በመሆን ሤራ አድርገዋል፤ እነርሱም ይሁዳን ለመውጋት፥ ሕዝቡንም አስጨንቀው የእነርሱ ደጋፊ በማድረግ የጣብኤልን ልጅ ሊያነግሡባቸው ወስነዋል።” ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህ ምክራቸው አይጸናም፤ ከቶ ሊሆን አይችልም፤ ስለምን ቢባል፥ የሶርያ ራስ ደማስቆ ስትሆን፥ የደማስቆም ራስ ረጺን ነው፤ ስለ እስራኤልም የሆነ እንደ ሆነ፥ በስልሳ አምስት ዓመቶች ጊዜ ውስጥ ብትንትናቸው ወጥቶ በመንግሥትነት መታወቃቸው ይቀራል። እንዲሁም የእስራኤል ራስ ሰማርያ ስትሆን፥ የሰማርያም ራስ ንጉሥ ፋቁሔ ነው። “ጽኑ እምነት ባይኖራችሁ እናንተም አትጸኑም።” እግዚአብሔር እንደገና አካዝን እንዲህ አለው፦ “ከምድር ጥልቀትም ሆነ ከሰማይ ከፍታ አንድ ምልክት እንዲሰጥህ አምላክህን እግዚአብሔርን ለምን።” አካዝ ግን “ምልክት ስጠኝ ብዬ አልጠይቅም፤ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ። ለዚህም ኢሳይያስ ሲመልስ እንዲህ አለ “እናንተ የንጉሥ ዳዊት ቤተሰብ ሆይ! ስሙ፤ ሰውን ማሰልቸታችሁ አንሶ እግዚአብሔርንስ ማሳዘን ትፈልጋላችሁን? እንግዲህ እግዚአብሔር ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ‘ዐማኑኤል’ ብላ ትጠራዋለች፤ እርሱም ክፉውን ነገር ትቶ መልካሙን ነገር ለመምረጥ የሚያስችል ዕውቀት በሚያገኝበት ጊዜ ማርና ወተት ይመገባል። ታዲያ፥ ይህ ሕፃን በጎውን ከክፉ ለይቶ ከማወቁ በፊት አንተ ትፈራቸው የነበሩ የእነዚህ የሁለት ነገሥታት ምድሮች ፈራርሰው ባድማ ይሆናሉ። “እነሆ እግዚአብሔር እስራኤል ከይሁዳ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቀውን የመከራ ዘመን በአንተና በሕዝብህ፥ በአባትህም ንጉሣዊ ቤተሰብ ላይ ያመጣል፤ ይኸውም የአሦርን ንጉሥ ያመጣብሃል ማለት ነው። “ያም ዘመን በደረሰ ጊዜ ከዓባይ ወንዝ ዳርቻ ርቀት ግብጻውያን እንደ ዝንብ መንጋ፥ አሦራውያንም ከአገራቸው እንደ ንብ ሠራዊት እየተመሙ ይመጡ ዘንድ እግዚአብሔር ምልክት ይሰጣቸዋል። እነርሱም እየተርመሰመሱ ወጥተው በበረሓው ሸለቆና በአለቱ ዋሻ ውስጥ በእሾኽ ቊጥቋጦና በከብት መሰማሪያ ግጦሽ ላይ ይሰፍራሉ። “ያም ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሠ ነገሥት የራሳችሁን የጢማችሁንና የሰውነታችሁን ሁሉ ጠጒር ይላጫል። “በዚያም ዘመን አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በጎች ይኖሩታል፤ እነርሱም ከሚሰጡት ብዙ ወተት የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ ያገኛል፤ ከዚህም የተነሣ በምድሪቱ ላይ የሚተርፉ ሰዎች ምግባቸው ማርና ወተት ይሆናል። “በዚያም ቀን ግምቱ ሺህ ብር የሚሆን አንድ ሺህ ምርጥ የወይን ተክል እንዲለማ የተደረገበት ቦታ ሁሉ ኲርንችትና እሾኽ ይበቅልበታል። አገሪቱ በኲርንችትና በእሾኽ የተሞላች ስለ ሆነች ሕዝቡ ለአደን የሚወጣው ቀስትና ፍላጻ ይዞ ነው። ቀድሞ በዶማ ተቈፍረው እህል ይበቅልባቸው የነበሩ ኰረብቶች ሁሉ ኲርንችትንና እሾኽን በመፍራት ማንም ወደዚያ አይሄድም፤ ነገር ግን የከብትና የበግ መንጋ መሰማሪያ ብቻ ይሆናሉ።”
ኢሳይያስ 7:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የዖዝያን የልጅ ልጅ፤ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፤ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም። ለዳዊት ቤት፤ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፤ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ። ጌታም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “‘አንተና ልጅህ ሸአር-ያሹብ አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኩሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤’” እንዲህም በለው፤ “‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጉማጆች፤ በሶርያና በንጉሷ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቁጣ አትሸበር።’ ሶርያ ኤፍሬምና፤ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤ ‘ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት።’ ልዑል እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤ ከቶም አይደረግም፤ የሶርያ ራስ ደማስቆ፤ የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤ በሥልሳ አምስት ዓመት ውስጥ፤ የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም ይቀራል። የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፤ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፤ ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ እንደገናም ጌታ አካዝን እንዲህ አለው፤ ‘ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከጌታ ከአምላክህ ለምን።’ አካዝ ግን፤ አልለምንም፤ ጌታንም አልፈታተንም” አለ። ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ፤ የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፤ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው። በዚያን ቀን ጌታ ራቅ ካሉት ከግብጽ ወንዞች ዝንቦችን፤ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። እነርሱም በሙሉ መጥተው፤ በየበረሓው ሸለቆ፤ በየዐለቱ ንቃቃት፤ በየእሾኩ ቁጥቋጦና በየውሃው ጉድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። በዚያን ቀን፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ፤ ማለትም በአሦር ንጉሥ፤ የራስና የእግር ጠጉራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። በዚያን ቀን፤ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። በዚያን ቀን ሺህ ሰቅል ብር የሚያወጣ አንድ ሺህ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፤ ኩርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። ምድሪቱ በኩርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፤ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ ኩርርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብታዎች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።”