ትንቢተ ኢሳይያስ 7
7
ለንጉሥ አካዝ የመጣለት መልእክት
1ከዖዝያን ልጅ ከኢዮአታም የተወለደው አካዝ በይሁዳ በነገሠበት ዘመን፥ የሶርያ ንጉሥ ረጺንና የእስራኤል ንጉሥ የረማልያ ልጅ ፋቁሔ ጦርነት ማስነሣት ፈልገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ነገር ግን ኢየሩሳሌምን ድል ሊያደርጉአት አልቻሉም። #2ነገ. 16፥5፤ 2ዜ.መ. 28፥5-6።
2ሶርያ ከእስራኤል መንግሥት ጋር በመተባበር የጦር ቃል ኪዳን መግባትዋን የይሁዳ ንጉሥ በሰማ ጊዜ እርሱና ሕዝቡ ደንግጠው ልባቸው በነፋስ እንደ ተመታ ዛፍ ተናወጠ።
3እግዚአብሔርም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፦ “አንተና ልጅህ ሼርያሹብ ንጉሥ አካዝን ለመገናኘት ውጡ፤ እርሱንም ከላይኛው ኩሬ ውሃ በሚመጣበት በልብስ አጣቢዎች ቦታ ታገኙታላችሁ። 4ረጋ እንዲል፤ እንዳይፈራ፥ በእሳት ተቀጣጥሎ እንደሚነድ እንደ ግንድ ጢስ በሆኑት በሬዚንና በሶርያው በሬማልያ ልጅ ምክንያት እንዳይሸበር ንገረው። 5በእርግጥ ሶርያውያን ከእስራኤላውያንና ከንጉሣቸው ጋር ግብረ አበር በመሆን ሤራ አድርገዋል፤ 6እነርሱም ይሁዳን ለመውጋት፥ ሕዝቡንም አስጨንቀው የእነርሱ ደጋፊ በማድረግ የጣብኤልን ልጅ ሊያነግሡባቸው ወስነዋል።”
7ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ይህ ምክራቸው አይጸናም፤ ከቶ ሊሆን አይችልም፤ 8ስለምን ቢባል፥ የሶርያ ራስ ደማስቆ ስትሆን፥ የደማስቆም ራስ ረጺን ነው፤ ስለ እስራኤልም የሆነ እንደ ሆነ፥ በስልሳ አምስት ዓመቶች ጊዜ ውስጥ ብትንትናቸው ወጥቶ በመንግሥትነት መታወቃቸው ይቀራል። 9እንዲሁም የእስራኤል ራስ ሰማርያ ስትሆን፥ የሰማርያም ራስ ንጉሥ ፋቁሔ ነው።
“ጽኑ እምነት ባይኖራችሁ እናንተም አትጸኑም።”
የዐማኑኤልን መምጣት የሚያሳይ ምልክት
10እግዚአብሔር እንደገና አካዝን እንዲህ አለው፦ 11“ከምድር ጥልቀትም ሆነ ከሰማይ ከፍታ አንድ ምልክት እንዲሰጥህ አምላክህን እግዚአብሔርን ለምን።”
12አካዝ ግን “ምልክት ስጠኝ ብዬ አልጠይቅም፤ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ።
13ለዚህም ኢሳይያስ ሲመልስ እንዲህ አለ “እናንተ የንጉሥ ዳዊት ቤተሰብ ሆይ! ስሙ፤ ሰውን ማሰልቸታችሁ አንሶ እግዚአብሔርንስ ማሳዘን ትፈልጋላችሁን? 14እንግዲህ እግዚአብሔር ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ‘ዐማኑኤል’ ብላ ትጠራዋለች፤ #7፥14 ዐማኑኤል፦ በዕብራይስጥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው። #ማቴ. 1፥23። 15እርሱም ክፉውን ነገር ትቶ መልካሙን ነገር ለመምረጥ የሚያስችል ዕውቀት በሚያገኝበት ጊዜ ማርና ወተት ይመገባል። 16ታዲያ፥ ይህ ሕፃን በጎውን ከክፉ ለይቶ ከማወቁ በፊት አንተ ትፈራቸው የነበሩ የእነዚህ የሁለት ነገሥታት ምድሮች ፈራርሰው ባድማ ይሆናሉ።
17“እነሆ እግዚአብሔር እስራኤል ከይሁዳ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቀውን የመከራ ዘመን በአንተና በሕዝብህ፥ በአባትህም ንጉሣዊ ቤተሰብ ላይ ያመጣል፤ ይኸውም የአሦርን ንጉሥ ያመጣብሃል ማለት ነው።
18“ያም ዘመን በደረሰ ጊዜ ከዓባይ ወንዝ ዳርቻ ርቀት ግብጻውያን እንደ ዝንብ መንጋ፥ አሦራውያንም ከአገራቸው እንደ ንብ ሠራዊት እየተመሙ ይመጡ ዘንድ እግዚአብሔር ምልክት ይሰጣቸዋል። 19እነርሱም እየተርመሰመሱ ወጥተው በበረሓው ሸለቆና በአለቱ ዋሻ ውስጥ በእሾኽ ቊጥቋጦና በከብት መሰማሪያ ግጦሽ ላይ ይሰፍራሉ።
20“ያም ዘመን በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሠ ነገሥት የራሳችሁን የጢማችሁንና የሰውነታችሁን ሁሉ ጠጒር ይላጫል።
21“በዚያም ዘመን አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በጎች ይኖሩታል፤ 22እነርሱም ከሚሰጡት ብዙ ወተት የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ ያገኛል፤ ከዚህም የተነሣ በምድሪቱ ላይ የሚተርፉ ሰዎች ምግባቸው ማርና ወተት ይሆናል።
23“በዚያም ቀን ግምቱ ሺህ ብር የሚሆን አንድ ሺህ ምርጥ የወይን ተክል እንዲለማ የተደረገበት ቦታ ሁሉ ኲርንችትና እሾኽ ይበቅልበታል። 24አገሪቱ በኲርንችትና በእሾኽ የተሞላች ስለ ሆነች ሕዝቡ ለአደን የሚወጣው ቀስትና ፍላጻ ይዞ ነው። 25ቀድሞ በዶማ ተቈፍረው እህል ይበቅልባቸው የነበሩ ኰረብቶች ሁሉ ኲርንችትንና እሾኽን በመፍራት ማንም ወደዚያ አይሄድም፤ ነገር ግን የከብትና የበግ መንጋ መሰማሪያ ብቻ ይሆናሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997