ትንቢተ ኢሳይያስ 8
8
የኢሳይያስ ልጅ ለሕዝቡ የምርኮ ምልክት መሆኑ
1እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ትልቅ ሰሌዳ ወስደህ በጉልህ ጽሑፍ ‘ለማጥፋትና ለምርኮ ፍጠን’ ብለህ ጻፍ። 2ታማኞች የሆኑ ሁለት ሰዎችን፥ ይኸውም ካህኑን ኦርዮንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርገህ አስቀምጣቸው።”
3ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከነቢይቱ ሚስቴ ጋር ተገናኘሁ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ስሙን ‘ለማጥፋትና ለምርኮ ፍጠን!’ ብለህ ጥራው 4ልጁም ገና ‘አባባና እማማ’ ብሎ ለመጥራት ከመቻሉ በፊት የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ተመዝብሮ ይወሰዳል።”
የአሶር ንጉሥ አመጣጥ
5እግዚአብሔር ዳግመኛ ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፤ 6“በጸጥታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ምንጭ ውሃ ትተው በንጉሥ ረጺንና በንጉሥ ፋቁሔ ተደስተዋል፤ 7አሁን እኔ የአሦርን ንጉሥ ከኀይለኛ ሠራዊቱ ጋር በእነርሱ ላይ አስነሣዋለሁ፤ የሠራዊቱም አመጣጥ የኤፍራጥስን ወንዝ ሞልቶ እንደሚያጥለቀልቅ ማዕበል ይሆናል። 8በኀይል እየጐረፈም ወደ ይሁዳ ምድር ይገባል፤ ሁሉን ነገር አጥለቅልቆ ከመሸፈን አልፎ ሙላቱ እስከ አንገት ይደርሳል፤” ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ እርሱም ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ሰውራ እንደምትጠብቅ ምድሪቱን ይጠብቃል።
9እናንተ አሕዛብ ጦርነትን ዐወጁ! ነገር ግን ትደመሰሳላችሁ፤ እናንተም የሩቅ አገር ሰዎች ሁሉ አድምጡ፤ ለጦርነትም ተዘጋጁ! ነገር ግን ትደመሰሳላችሁ፤ አሁንም ለጦርነት ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ትደመሰሳላችሁ። 10የጦር ዕቅድንም አውጡ፤ ነገር ግን እናንተ እንዳሰባችሁት አይሳካላችሁም፤ የፈለጋችሁትን ያኽል ተናገሩ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለ ሆነ ምክራችሁ አይጸናም።
እግዚአብሔር ነቢዩን እንዳስጠነቀቀው
11ሕዝቡ በሄደበት መንገድ እንዳልሄድ እግዚአብሔር በብርቱ ኀይሉ እንዲህ ብሎ አስጠነቀቀኝ፤ 12“እነርሱ የዐመፅ ሤራ ነው የሚሉትን እናንተም የዐመፅ ሤራ ነው አትበሉ፤ እናንተ እነርሱ የሚፈሩትን ነገር አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 13እኔ የሠራዊት አምላክ ቅዱስ እንደ ሆንኩ አስቡ፤ መፍራት የሚገባችሁም እኔን ብቻ ነው። #1ጴጥ. 3፥14-15። 14ከቅድስናዬ ልዕልና የተነሣ ለይሁዳና ለእስራኤል የማሰናከያ ድንጋይና የመውደቂያ አለት እንዲሁም ለኢየሩሳሌም ሕዝብ ወጥመድ እሆንባቸዋለሁ። 15ስለዚህ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ ወድቀውም ይሰባበራሉ፤ በወጥመድ ተይዘውም ይወሰዳሉ።” #1ጴጥ. 2፥8።
ለጠንቋዮችና ለሙታን ጠሪዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
16ምስክርነቱን ጠብቀህ ያዝ፤ በደቀ መዛሙርቴ ልብ ውስጥም ሕጉን አትም። 17ምንም እንኳ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ ፊቱን ቢመልስባቸውም እኔ በእርሱ ላይ እተማመናለሁ። #ዕብ. 2፥13።
18እነሆ፥ ልጆቼና እኔ በጽዮን ተራራ ላይ ከሚኖረው ከሠራዊት አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጠን የማስጠንቀቂያ ምልክት ነን።
19“በመንተባተብ የሚቀባጥሩትን ሟርተኞችንና የሙታን መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ” እያሉ የሚሰብኩአችሁ ወገኖች አሉ፤ ታዲያ፥ ስለ ሕያዋን ሙታንን ከመጠየቅ ይልቅ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን?
20ይህን ቃል ባይናገሩ በእርግጥ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም።
የመከራ ጊዜ
21ሕዝቡ ተስፋ ቈርጠውና ተርበው በምድሪቱ ላይ ይንከራተታሉ፤ ከመራባቸው የተነሣ ተበሳጭተው ወደ ሰማይ እያንጋጠጡ ንጉሣቸውንና አማልክታቸውን ይራገማሉ። 22ከዚያ በኋላ ወደ ምድር ሲመለከቱ ሊያዩ የሚችሉት ጭንቀት ጨለማና ጭፍግግ ያለ አስፈሪ ሁኔታን ነው፤ ወደ ድቅድቅ ጨለማም ይጣላሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997