የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 6

6
እግዚአብሔር ኢሳይያስን ለነቢይነት እንደ ጠራው
1ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን አየሁት፤ እርሱም ከፍ ባለና ልዕልና ባለው ዙፋን ላይ ተቀምጦ መጐናጸፊያውም ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። #2ነገ. 15፥7፤ 2ዜ.መ. 26፥23። 2ሱራፌል ተብለው የሚጠሩ መላእክትም በዙሪያው ነበሩ፤ እያንዳንዱ መልአክ ስድስት ክንፍ አለው፤ በሁለቱ ክንፎቹ ፊቱን ይሸፍናል፤ በሁለቱ ክንፎቹ እግሮቹን ሸፍኖ በሁለት ክንፎቹ ይበር ነበር፤ 3አንዱ መልአክ ከሌላው ጋር በመቀባበል፥
“የሠራዊት አምላክ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ ነው!
ክብሩም በዓለም ሁሉ የተሞላ ነው!” ይሉ ነበር።
# ራዕ. 4፥8። 4ከድምፃቸው ጩኸት የተነሣ የቤተ መቅደሱ መድረክ እስከ ሥር መሠረቱ ተናወጠ፤ ቤተ መቅደሱም በጢስ ተሞላ። #ራዕ. 15፥8።
5እኔም “እነሆ አንደበቶቹ በረከሱበት ሕዝብ መካከል የምኖር፥ አንደበቴም የረከሰብኝ ሰው ነኝ፤ ንጉሡን የሠራዊት አምላክን በዐይኖቼ አይቼአለሁና መጥፋቴ ስለ ሆነ ወዮልኝ!” አልኩ።
6ከነዚያም መላእክት አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፤ ከመሠዊያው የወሰደው የእሳት ፍም የያዘበት ጒጠት በእጁ ነበር። 7በእሳቱም ፍም ከንፈሮቼን ነክቶ “እነሆ ይህ የእሳት ፍም ከንፈሮችህን ስለ ነካ በደልህ ተወግዶልሃል፤ ኃጢአትህም ይቅር ተብሎልሃል” አለኝ።
8ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር “ማንን እልካለሁ? መልእክተኛ የሚሆንልንስ ማን ነው?” ሲል ሰማሁት፤ እኔም “እነሆ እኔ እሄዳለሁ! እኔን ላከኝ!” አልኩ።
9እርሱም “እንግዲያውስ ወደዚህ ሕዝብ ሂድና ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ ነገር ግን ልብ አታደርጉም’ በላቸው” አለኝ። 10ቀጥሎም “እንዳያዩ፥ እንዳይሰሙና እንዳያስተውሉ በዓይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸው አስተውለው ወደ እኔ ተመልሰው እንዳይፈወሱ ይህን ሕዝብ ልቡ የደነደነ፥ ጆሮው የተደፈነ፥ ዐይኑም የተጨፈነ እንዲሆን አድርግ” አለኝ። #ማቴ. 13፥14-15፤ ማር. 4፥12፤ ሉቃ. 8፥10፤ ዮሐ. 12፥40፤ ሐ.ሥ. 28፥26-27።
11እኔም “አቤቱ ጌታ ሆይ፥ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?” ብዬ ጠየቅሁ።
እርሱም “ከተሞች እስኪፈርሱ፥ ቤቶችም የሚኖርባቸው አጥተው ወና እስኪሆኑና አገሪቱም የተፈታች ባድማ እስክትሆን ድረስ ነው። 12ሕዝቡን ወደ ሩቅ አገር እሰዳለሁ፤ አገሪቱም ባድማ ትሆናለች። 13ከዐሥሩ አንድ ክፍል ቢተርፍም እንኳ እርሱም እንደ ግራር ወይም እንደ ዋርካ እንደገና ይቃጠላል። ዛፉ ሲቈረጥ ጉቶው ይቀራል። ጉቶውም የተቀደሰ ዘር ነው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ