የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 7:1-25

ትንቢተ ኢሳይያስ 7:1-25 አማ54

እንዲህም ሆነ፥ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፥ ሊያሸንፉአትም አልቻሉም። ለዳዊትም ቤት፦ ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል የሚል ወሬ ተነገረ፥ የእርሱም ልብ የሕዝቡ ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ። እግዚአብሔርም ኢሳይያስን አለው፦ አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፥ እንዲህም በለው፦ ተጠበቅ፥ ዝምም በል፥ ስለ እነዚህ ስለሚጤሱ ስለ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፥ ስለ ሶርያና ስለ ረአሶን ስለ ሮሜልዩም ልጅ ቍጣ አትፍራ፥ ልብህም አይድከም። ሶርያና ኤፍሬም የሮሜልዩም ልጅ፦ ወደ ይሁዳ እንውጣ እናስጨንቀውም፥ እንስበረውም፥ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት ብለው ክፋት ስለ መከሩብህ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም። የሶርያ ራስ ደማስቆ ነው፥ የደማስቆም ራስ ረአሶን ነው፥ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራልና ሕዝብ አይሆንም፥ የኤፍሬምም ራስ ሰማርያ ነው፥ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። ባታምኑ አትጸኑም። እግዚእብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለምን። አካዝም፦ አልለምንም፥ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም አለ። እርሱም አለ፦ እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፥ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፥ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፥ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። ሕፃኑም ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች። እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፥ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ እግዚአብሔር በግብፅ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝምብ በአሦርም አገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል። ይመጡማል፥ እነርሱም ሁሉ በበረሐ ሸለቆ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በእሾህ ቍጥቋጦ ሁሉ ላይ በማሰማርያውም ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ። በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፥ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይበላል። በዚያን ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ሰው አንዲት ጊደርን ሁለት በጎችንም ያሳድጋል፥ ከሚሠጡት ወተት ብዛት የተነሣ ቅቤ ይበላል፥ በአገሪቱም መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል። በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ ሺህ ብር የተገመተ ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ሥፍራ ሁሉ ለኵርንችትና ለእሾህ ይሆናል። ኵርንችትና እሾህ በምድር ሁሉ ላይ ነውና በፍላጻና በቀስት ወደዚያ ይገባሉ። በመቈፈርያም ወደ ተቈፈሩ ኮረብቶች ሁሉ ከኵርንችትና እሾህ ፍርሃት የተንሣ ወደዚያ አትሄድም፥ ነገር ግን የበሬ ማሰማርያና የበግ መራገጫ ይሆናል።