ትንቢተ ኢሳይያስ 7
7
ለንጉሥ አካዝ የመጣለት መልእክት
1 #
2ነገ. 16፥5፤ 2ዜ.መ. 28፥5፤6። የዖዝያን የልጅ ልጅ፤ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፤ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም። 2ለዳዊት ቤት፤ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፤ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ። 3ጌታም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “‘አንተና ልጅህ ሸአር-ያሹብ አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኩሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤’” 4እንዲህም በለው፤ “‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጉማጆች፤ በሶርያና በንጉሷ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቁጣ አትሸበር።’ 5ሶርያ ኤፍሬምና፤ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤ 6‘ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት።’ 7ልዑል እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤ ከቶም አይደረግም፤ 8የሶርያ ራስ ደማስቆ፤ የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤ በሥልሳ አምስት ዓመት ውስጥ፤ የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም ይቀራል። 9የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፤ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፤ ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ 10እንደገናም ጌታ አካዝን እንዲህ አለው፤ 11‘ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከጌታ ከአምላክህ ለምን።’ 12አካዝ ግን፤ አልለምንም፤ ጌታንም አልፈታተንም” አለ። 13ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ፤ የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? 14#ማቴ. 1፥23።ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። 15ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። 16ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። 17ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፤ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው። 18በዚያን ቀን ጌታ ራቅ ካሉት ከግብጽ ወንዞች ዝንቦችን፤ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። 19እነርሱም በሙሉ መጥተው፤ በየበረሓው ሸለቆ፤ በየዐለቱ ንቃቃት፤ በየእሾኩ ቁጥቋጦና በየውሃው ጉድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። 20በዚያን ቀን፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ፤ ማለትም በአሦር ንጉሥ፤ የራስና የእግር ጠጉራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። 21በዚያን ቀን፤ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። 22ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። 23በዚያን ቀን ሺህ ሰቅል ብር የሚያወጣ አንድ ሺህ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፤ ኩርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። 24ምድሪቱ በኩርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፤ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ 25ኩርርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብታዎች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ