ኢሳይያስ 65:17-22
ኢሳይያስ 65:17-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይሆናልና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በውስጥዋ ደስታንና ሐሤትን ያገኛሉ፤ እኔም ለኢየሩሳሌም ደስታን ለሕዝቤም ሐሤትን አደርጋለሁ። እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤትን አደርጋለሁ፤ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ በውስጥዋ አይሰማም። ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጐልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ ኀጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና። ቤቶችንም ይሠራሉ፤ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፤ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ሕይወት ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረዥም ዘመን ደስ ይላቸዋል።
ኢሳይያስ 65:17-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እነሆ፤ እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም። ነገር ግን በምፈጥረው፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ። ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣ ሕዝቧን ለሐሤት እፈጥራለሁና። በኢየሩሳሌም እደሰታለሁ፤ በሕዝቤ ሐሤት አደርጋለሁ፤ የልቅሶና የጩኸት ድምፅ፣ ከእንግዲህ በዚያ አይሰማም። “ከእንግዲህም በዚያ፣ ለጥቂት ጊዜ ብቻ በሕይወት የሚኖር ሕፃን፣ ወይም ዕድሜ ያልጠገበ አረጋዊ አይኖርም፤ አንድ መቶ ዓመት የሞላው ሰው ቢሞት፣ በዐጭር እንደ ተቀጨ ይቈጠራል፤ አንድ ሰው መቶ ዓመት ሳይሞላው ቢሞት፣ እንደ ተቀሠፈ ይገመታል። ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ፣ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይረዝማል፤ እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።
ኢሳይያስ 65:17-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፥ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ወደ ልብም አይገቡም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፥ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፥ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም። ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፥ ጕልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ ኃጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና። ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፥ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፥ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።
ኢሳይያስ 65:17-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ እኔ አዳዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ከዚህ በፊት የነበሩት ሁሉ ይረሳሉ፤ አይታሰቡምም። እኔ ኢየሩሳሌምን ለደስታ ሕዝብዋንም ሐሴተኞች እንዲሆኑ ልፈጥር ስለ ሆነ ለዘለዓለም ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ። እኔም ራሴ በኢየሩሳሌምና በሕዝቤ ደስ ይለኛል፤ ከዚያም በኋላ ለቅሶም ሆነ የዋይታ ድምፅ አይኖርም። በሕፃንነቱ የሚሞት ከቶ አይኖርም፤ ዕድሜውንም የማይፈጽም ሽማግሌ አይኖርም፤ በመቶ ዓመቱ የሚሞት ሰው በወጣትነቱ እንደ ሞተ ወጣት ከመቶ ዓመት በታች የሚሞት ሰው እንደ ተረገመ ይቈጠራል። ሕዝቤ ቤት ሠርተው ይኖሩበታል፤ ወይን ተክለው ፍሬውን ይበላሉ፤ እነርሱ የሠሩትን ቤት ሌሎች አይገቡበትም፤ የተከሉትንም ማንኛውንም ነገር ባዕዳን አይበሉትም፤ ሕዝቤ እንደ ዛፍ ለረጅም ዘመናት ይኖራሉ፤ የመረጥኳቸውም ሰዎች የደከሙበትን ነገር ለረጅም ጊዜ ይደሰቱበታል።
ኢሳይያስ 65:17-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁ፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ትውስታቸውም አይኖርም። ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘለዓለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም። ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጎልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ የመቶ ዓመት ሳይሆነው የሚሞት እንደተረገመ ኃጢአተኛ ይታያል። ቤትም ይሠራሉ ይኖሩበታል፤ ወይንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።