የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 65

65
የእግዚአብሔር ዳኝነትና አዳኝነት
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔን ላልጠየቁኝ ተገለጥኩላቸው፤ ላልፈለጉኝም ተገኘሁላቸው፤ ስሜንም ላልጠራ ሕዝብ ‘እነሆ፥ እዚህ አለሁ፥ እነሆ፥ እዚህ አለሁ’ አልኳቸው። #ሮም 10፥20። 2የራሱን ክፉ ሐሳብ በመከተል መልካም በሆነ መንገድ ለማይመራ፥ ዐመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ። #ሮም 10፥21። 3እነዚህም ሰዎች በአትክልት ቦታ ውስጥ መሥዋዕት በመሠዋትና በጡብ ላይ በፊቴ ሁልጊዜ ዕጣን በማጠን እኔን የሚያስቈጡኝ ናቸው። 4እንዲሁ እነርሱ በመቃብሮች መካከል የሚቀመጡ፥ በድብቅ ቦታዎች ሌሊቱን የሚያሳልፉ፥ የእሪያ ሥጋ የሚበሉ፥ በዕቃቸውም ውስጥ የረከሰ ወጥ የሚያኖሩ ናቸው። 5እነርሱ፥ ‘እኛ ቅዱሳን ስለ ሆንን ወደ እኛ አትቅረቡ!’ የሚሉ ናቸው፤ እነዚህ ነገሮች ቀኑን ሙሉ ለሚነድ እሳት ኀይለኛ ቊጣዬን የሚያቀጣጥሉ ናቸው።
6“እነሆ፥ በፊቴ ተመዝግቦአል፤ በእርግጥ በሙሉ እከፍላቸዋለሁ እንጂ ዝም አልልም።” 7እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በተራሮች ላይ መሥዋዕት በማቅረባቸውና ስሜን ባለማክበራቸው ስለ እነርሱና ስለ አባቶቻቸው በደል ዋጋቸውን በሙሉ እከፍላቸዋለሁ።”
8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ወይን ጠጅ ከወይን ዘለላ እንደሚገኝና ‘በረከት ስላለበት አታጥፉት’ እንደሚባል እኔም በዚሁ ዐይነት ስለ አገልጋዮቼ ስል ሕዝቡን በሙሉ አላጠፋም። 9ለያዕቆብ ልጆችን እሰጠዋለሁ፤ ይሁዳንም የተራሮቼን ርስት ወራሽ አደርገዋለሁ፤ እኔ የመረጥኩት ምድሪቱን ይይዛል፤ አገልጋዮቼም በዚያ ይኖራሉ። 10እኔን ለሚፈልጉ ወገኖቼ ሳሮን ለበግ መንጋዎች ማሰማሪያ፥ የአኮር ሸለቆ ለከብቶች መንጋ መመሰጊያ ይሆናሉ። #ኢያሱ 7፥24-25።
11“እኔን እግዚአብሔርን ትታችሁ የተቀደሰ ተራራዬን በመርሳት ‘መልካም አጋጣሚ’ ለተባለ ጣዖትም ማእድ ታዘጋጃላችሁ፤ ‘ዕድል ፈንታ’ ለተባለ ጣዖትም ዋንጫችሁን በተደባለቀ የወይን ጠጅ ትሞላላችሁ። 12ስለዚህ እናንተ በጠራኋችሁ ጊዜ መልስ ስላልሰጣችሁና በተናገርኩም ጊዜ ስላላዳመጣችሁ ለእኔ መታዘዝን ትታችሁ ክፉ ማድረግን ስለ መረጣችሁ ዕድል ፈንታችሁ ለገዳይ ተንበርክኮ በሰይፍ መገደል ይሆናል።” 13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “አገልጋዮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ አገልጋዮቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ አገልጋዮቼ ይደሰታሉ፤ እናንተ ግን ኀፍረት ይደርስባችኋል። 14አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፤ እናንተ ግን ከልብ ሐዘን የተነሣ ታላቅሳላችሁ፤ ከመንፈስም ጭንቀት የተነሣ ዋይ፥ ዋይ ትላላችሁ። 15እኔ ጌታ እግዚአብሔርም እናንተን ለሞት አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ የእናንተም ስም በእኔ ተመራጮች ዘንድ መራገሚያ ይሆናል፤ ለአገልጋዮቼ ግን የተለየ ስም እሰጣቸዋለሁ። 16የቀድሞው ችግር ስለ ተረሳና ከዐይኔ ስለ ተሰወረ በሀገሪቱ በረከትን የሚለምን በእኔ በታማኙ እግዚአብሔር ስም ይለምናል፤ በሀገሪቱም የሚምሉ በእኔ በታማኙ እግዚአብሔር ስም ይምላሉ።”
አዲስ ፍጥረት
17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ እኔ አዳዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ከዚህ በፊት የነበሩት ሁሉ ይረሳሉ፤ አይታሰቡምም። 18እኔ ኢየሩሳሌምን ለደስታ ሕዝብዋንም ሐሴተኞች እንዲሆኑ ልፈጥር ስለ ሆነ ለዘለዓለም ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ። 19እኔም ራሴ በኢየሩሳሌምና በሕዝቤ ደስ ይለኛል፤ ከዚያም በኋላ ለቅሶም ሆነ የዋይታ ድምፅ አይኖርም። #ራዕ. 21፥4። 20በሕፃንነቱ የሚሞት ከቶ አይኖርም፤ ዕድሜውንም የማይፈጽም ሽማግሌ አይኖርም፤ በመቶ ዓመቱ የሚሞት ሰው በወጣትነቱ እንደ ሞተ ወጣት ከመቶ ዓመት በታች የሚሞት ሰው እንደ ተረገመ ይቈጠራል። 21ሕዝቤ ቤት ሠርተው ይኖሩበታል፤ ወይን ተክለው ፍሬውን ይበላሉ፤ 22እነርሱ የሠሩትን ቤት ሌሎች አይገቡበትም፤ የተከሉትንም ማንኛውንም ነገር ባዕዳን አይበሉትም፤ ሕዝቤ እንደ ዛፍ ለረጅም ዘመናት ይኖራሉ፤ የመረጥኳቸውም ሰዎች የደከሙበትን ነገር ለረጅም ጊዜ ይደሰቱበታል። 23ሥራቸው ከንቱ አይሆንም፤ የወለዱአቸው ልጆችና የልጅ ልጆቻቸው በእግዚአብሔር የተባረኩ ስለሚሆኑ ልጆቹን የሚወልዱት ጥፋት እንዲደርስባቸው አይደለም። 24እኔን በልመና ከመጥራታቸው በፊት እመልስላቸዋለሁ፤ እየጸለዩም ሳለ እሰማቸዋለሁ። 25ተኲላና ጠቦት አብረው ይመገባሉ፤ አንበሳ እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤ የእባብ ምግብ ትቢያ ይሆናል፤ እነርሱም በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፤ አያጠፉምም” ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። #ኢሳ. 11፥6-9።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ