የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 64

64
1ምነው ሰማያትን ከፍተህ ብትወርድ፤ ተራራዎችም አንተን አይተው ምነው በተንቀጠቀጡ፤ 2እሳት ደረቁን እንጨት በሚያጋይ ጊዜ ፍሙ የተጣደውን ውሃ እንደሚያፍለቀልቀው፥ ሕዝቦችም በአንተ መገለጥ እንዲንቀጠቀጡ ወርደህ ስምህ በጠላቶችህ ዘንድ እንዲታወቅ አድርግ! 3ከዚህ በፊትም መጥተህ እኛ ያልጠበቅናቸውን እጅግ አስፈሪ የሆኑ ነገሮችን በፈጸምክበት ጊዜ ተራራዎች አንተን አይተው በፍርሃት ተንቀጠቀጡ። 4ከጥንት ጀምሮ ተስፋቸውን በእርሱ አድርገው ለሚተማመኑበት ወገኖች እነዚያን ሁሉ ድንቅ ነገሮች ያደረገ አምላክ ከአንተ በቀር አልተሰማም፤ አልታየም፤ የተረዳም የለም። #1ቆሮ. 2፥9። 5የአንተን መንገድ አስታውሰው ፈቃድህን በደስታ የሚፈጽሙትን ትረዳቸዋለህ፤ ፈቃድህን መተላለፍን በቀጠልን ጊዜ ግን አንተ ተቈጣኸን፤ ታዲያ እንዴት ልንድን እንችላለን? 6እኛ ሁላችን በኃጢአት ረክሰናል፤ ጽድቃችንም እንደ አደፍ ጨርቅ ሆኖአል፤ ከኃጢአታችን ብዛት የተነሣ ደርቀው በነፋስ እንደሚረግፉ ቅጠሎች ሆነናል። 7በኃጢአታችን ምክንያት ፊትህን ስላዞርክብንና ለበደላችንም ተገዢዎች እንድንሆን ስለ ተውከን ስምህን የሚጠራና አንተን ለማግኘት የሚጥር ማንም የለም።
8ሆኖም አምላክ ሆይ! አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ሸክላዎች ስንሆን አንተ ሠሪአችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን። 9አምላክ ሆይ! አምርረህ አትቈጣ፤ ኃጢአታችንንም ለዘለዓለም አታስብብን፤ እኛ ሁላችን ሕዝብህ መሆናችንን አስታውስ። 10የተቀደሱ ከተሞችህ በረሓ ሆነዋል፤ ጽዮን በረሓ ኢየሩሳሌምም ባድማ ሆነዋል። 11የቀድሞ አባቶቻችን አንተን ሲያመሰግኑበት የነበረ፥ ቅዱስና ውብ የሆነው ቤተ መቅደስህ በእሳት ጋይቶአል፤ የሚያስደስቱ ነገሮች ሁሉ ፈራርሰዋል። 12አምላክ ሆይ! ከዚህ ሁሉ በኋላ አንዳች ነገር አታደርግምን? ዝም ብለህስ በኀይለኛ ቅጣት ትቀጣናለህን?

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ