ትንቢተ ኢሳይያስ 66
66
የእግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ፈራጅነት
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ ታዲያ ለእኔ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ? የማርፍበትስ ቦታ ምን ዐይነት ነው? #ማቴ. 5፥34-35፤ 23፥22። 2እነዚህን ሁሉ ነገሮች የፈጠርኩ እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ሁሉም የእኔ ናቸው፤ እኔ የምመለከተው ልባቸው ወደ ተሰበረ፥ ትሑት መንፈስ ወዳላቸውና፥ ቃሌንም ወደሚያከብሩ ነው። #ሐ.ሥ. 7፥49-50።
3“ለእኔ በሬ ሲሠዉ በሌላ በኩል የሰውን ሕይወት ያጠፋሉ፤ ለእኔ ጠቦት ሲሠዉ ለጣዖትም ውሻ ያቀርባሉ፤ ለእኔ የእህል መሥዋዕት ሲያቀርቡ፤ የዕሪያ ደምም ለጣዖት ያቀርባሉ፤ ለእኔ ዕጣን ያጥናሉ፤ ጣዖቶቻቸውንም ያመሰግናሉ፤ የራሳቸውን አካሄድ በመምረጥ በርኲሰታቸው ይደሰታሉ። 4ስጠራ ማንም ስላልመለሰልኝ፥ ስናገር ማንም ስላላዳመጠኝ ነገር በፊቴ ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጉና የማያስደስተኝን ስለ መረጡ እኔም በእነርሱ ላይ ቅጣት አመጣባቸዋለሁ።”
5ቃሉን የምታከብሩ እናንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፦ “ስለ ስሜ የሚጠሉአችሁና የሚያገሉአችሁ እንዲህ ይሉአችኋል፦ ‘እናንተ ስትደሰቱ እናይ ዘንድ እስቲ እግዚአብሔር ክብሩን ይግለጥ፤’ ኀፍረት ላይ የሚወድቁት ግን እነርሱ ራሳቸው ናቸው። 6በከተማ የሚሰማውን ሁካታ አድምጡ! ከቤተ መቅደስም ድምፅ ስሙ፤ ይህም እኔ እግዚአብሔር ለጠላቶቼ ተገቢ ዋጋቸውን በምሰጥበት ጊዜ የሚሰማ ድምፅ ነው።” 7ጽዮን ምጥ ሳይጀምራት እንደ ወለደች፥ የምጥ ስሜት ሳይሰማት እንደ ተገላገለች ሴት ነች። #ራዕ. 12፥5። 8እንዲህ ያለ ነገር የሰማ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ያየ ማነው? አንድ አገር በአንድ ቀን፥ አንድ ሕዝብ በቅጽበት ሊወለዱ ይችላሉን? ይሁን እንጂ ጽዮን ምጥ እንደ ያዛት ወዲያውኑ ልጆችዋን ወልዳለች። 9እግዚአብሔር አምላካችሁ እንዲህ ይላል፦ “የመውለጃዋ ጊዜ እንዲደርስ ያደረግኋትን ሴት ልጅዋን እንዳትወልድ አደርጋለሁን? እንድትፀንስ ያደረግኋትን ሴት ማሕፀኗን እዘጋለሁን?
10የምትወዷት ሁሉ ከኢየሩሳሌም ጋር ደስ ይበላችሁ!
ስለ እርስዋም ሐሴት አድርጉ!
ያለቀሳችሁላት ሁሉ ስለ እርስዋ ተደሰቱ!
11ይህንንም የምታደርጉት ከመጽናኛ ጡትዋ ጠብታችሁ ትጠግቡ ዘንድ፥ ከተከበረው ደረትዋ የተትረፈረፈውን ወተት ጠጥታችሁ ትደሰቱ ዘንድ ነው።”
12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሀብትዋን እንደ ወንዝ ውሃ አበዛዋለሁ፤ የሕዝቦችንም ሀብት እንደ ወንዝ ጅረት አደርገዋለሁ፤ በክንድዋም ተይዛችሁ ትጠባላችሁ፤ በጭንዋም ላይ አድርጋ ትንከባከባችኋለች። 13እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እኔም እናንተን አጽናናችኋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ትጽናናላችሁ። 14ይህም ሲፈጸም በምታዩበት ጊዜ ሐሴት ታደርጋላችሁ፤ ሰውነታችሁም እንደ ሣር ይለመልማል፤ የእግዚአብሔር ኀይል ከአገልጋዮቹ ጋር፥ ቊጣው ግን በሚጠሉት ላይ እንደሚሆን ይታወቃል።” 15እግዚአብሔር በኀይለኛ ቊጣው ለመበቀልና በሚንበለበለው እሳት ለመገሠጽ በእሳት ሆኖ ይመጣል፤ መንኲራኲሮችም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው። 16እግዚአብሔር በሰዎች ሁሉ ላይ በእሳትና በሰይፍ ይፈርዳል፤ እንዲሁም በሞት የሚቀጣቸው ብዙዎች ናቸው።
17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእርያ ሥጋና አይጥ፥ እንዲሁም ሌሎች አጸያፊ ነገሮች ከሚበሉት ሰዎች መካከል አንዱን ተከትለው ወደ አትክልቶቹ ቦታዎች ለመሄድ ራሳቸውን የሚለዩና የሚያነጹ በአንድነት ይጠፋሉ። 18እኔ ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ የተለያየ ቋንቋ ያላቸውን ሕዝቦች ሁሉ እሰበስባለሁ፤ መጥተውም የእኔን ክብር ያያሉ። 19በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፤ ከሞት ከተረፉት መካከል ስለ እኔ ወዳልሰሙትና ክብሬንም ወዳላዩት ወደ ተለያዩ ሕዝቦች ወደ ተርሴስ፥ ወደ ሊብያውያን ቀስት ወደሚያስፈነጥሩ ወደ ሊድያውያን፥ ወደ ቱባል፥ ወደ ግሪክ፥ ራቅ ብለው ወደሚገኙት ደሴቶችም እልካቸዋለሁ፤ እነርሱም በሕዝቦች መካከል ክብሬን ይገልጣሉ። 20ወንድሞቻችሁን ሁሉ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቅዱስ ተራራዬ በፈረሶች፥ በሠረገሎች፥ በጋሪዎች፥ በበቅሎዎችና በግመሎች አድርገው ከተለያዩ አገሮች ለእግዚአብሔር እንደ መባ ያመጡአቸዋል፤ እነርሱንም የሚያመጡአቸው እስራኤላውያን የእህል ቊርባንን በሥርዓት በነጻ ዕቃ ለእኔ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ አድርገው ነው፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 21እኔም ከእነርሱ አንዳንዶቹን ካህናትና ሌዋውያን ሆነው እንዲያገለግሉ አደርጋቸዋለሁ።
22“የምፈጥራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በእኔ ጸንተው እንደሚኖሩ እንዲሁም ዘራችሁና ስማችሁ በእኔ ጸንተው ይኖራሉ፤ #ኢሳ. 65፥17፤ 2ጴጥ. 3፥13፤ ራዕ. 21፥1። 23ከወር መባቻ እስከ ሌላ የወር መባቻ በዓልና ከሰንበት እስከሚቀጥለው ሰንበት ሕዝብ ሁሉ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ሊሰግዱልኝ ይመጣሉ”፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 24“ወጥተው ሲሄዱም በእኔ ላይ በማመፃቸው የተገደሉትን ሰዎች በድን ያያሉ፤ እነርሱን የሚበላቸው ትል አይሞትም፤ የሚያቃጥላቸውም እሳት አይጠፋም፤ እነርሱንም የሚያያቸው የሰው ዘር ሁሉ ይጸየፋቸዋል።” #ማር. 9፥48።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 66: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997