ትንቢተ ኢሳይያስ 65
65
እግዚአብሔር ዐመፀኞችን እንደሚቀጣ
1ያልፈለጉኝ አገኙኝ፤ ላልጠየቁኝም ተገኘሁ፤ ስሜን ላልጠራ ሕዝብ፥ “እነሆኝ” አልሁት። 2በጽድቅ መንገድ ወደማይሄዱ፥ ኀጢአታቸውን ወደሚከተሉ ዐመፀኞች ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆችን ዘረጋሁ። 3እኒህ ሕዝብ ዘወትር የሚያስቈጡኝ ናቸው፤ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ በጡብም ላይ ለአጋንንት የሚያጥኑ፥ 4በመቃብርም መካከል የሚተኙ፥ በዋሻ ውስጥ የሚያልሙ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። የመሥዋዕታቸውን ደምና ዕቃቸውንም ሁሉ ያረክሳሉ። 5“እኔ ንጹሕ ነኝና ከእኔ ራቁ፥ ወደ እኔም አትቅረቡ” ይላሉ። ስለዚህም የቍጣዬ ጢስ በዘመኑ ሁሉ እንደ እሳት ይነድድባቸዋል። 6እነሆ፥ በፊቴ ተጽፎአል፦ ኀጢአቶቻችሁንና የአባቶቻችሁን ኀጢአት በአንድ ላይ ወደ ብብታቸው ፍዳ አድርጌ እመልሳለሁ እንጂ ዝም አልልም፤ ይላል እግዚአብሔር፤ 7በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ አሽሟጠጡኝ ስለዚህ አስቀድመው የሠሩትን ሥራቸውን በብብታቸው እሰፍራለሁ።
8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የወይን ፍሬ በዘለላው በተገኘች ጊዜ፦ በረከት በእርስዋ ላይ አለና አታጥፉት እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፋ ስለ ባሪያዎች እንዲህ አደርጋለሁ። 9የያዕቆብን ዘርና የይሁዳን ዘር አመጣለሁ፤ የተቀደሰው ተራራዬንም ይወርሳሉ፤ እኔ የመረጥኋቸውና ባሪያዎችም ይወርሱአታል፤ በዚያም ይኖራሉ። 10በመንጋው መሰማሪያና በዛፍ መካከል በአኮር ሸለቆና በቆላውም የላሞች መመሰግያ ለፈለጉኝ ሕዝቤ ይሆናል።
11“እናንተ ግን እኔን ተዋችሁኝ፤ ቅዱሱንም ተራራዬን ረሳችሁ፥ ለአጋንንትም ማዕድ አዘጋጃችሁ፤ ዕድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ቀዳችሁ፤ 12እኔም ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ ሁላችሁም በሰይፍ ትገደላላችሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገር አደረጋችሁ፤ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራኋችሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና።”
13ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ ባሪያዎች ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎች ይጠጣሉ፤ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎች ደስ ይላቸዋል፤ እናንተ ግን ትጐሰቍላላችሁ፤ 14እነሆ፥ ባሪያዎች ሐሤት ያደርጋሉ፤ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ! ትላላችሁ። 15ስማችሁንም እኔ ለመረጥኋቸው ሕዝቤ ጥጋብ#ዕብ. “ርግማን” ይላል። አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፤ ጌታ እግዚአብሔርም ያጠፋችኋል፤ ባሪያዎች ግን በሐዲስ ስም ይጠራሉ። 16እንዲሁም በምድር ላይ የተባረኩ ይሆናሉ፤ እውነተኛውን አምላክ ያመሰግናሉና፥ በምድርም ላይ በእውነተኛው አምላክ ይምላሉና፤ የቀድሞውንም ጭንቀት ረስተዋልና፤ በልቡናቸውም አያስቡትምና።
17“እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ይሆናልና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም። 18ነገር ግን በውስጥዋ ደስታንና ሐሤትን ያገኛሉ፤ እኔም ለኢየሩሳሌም ደስታን ለሕዝቤም ሐሤትን አደርጋለሁ። 19እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤትን አደርጋለሁ፤ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ በውስጥዋ አይሰማም። 20ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጐልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ ኀጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና። 21ቤቶችንም ይሠራሉ፤ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። 22ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፤ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ሕይወት ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረዥም ዘመን ደስ ይላቸዋል። 23እነርሱ ከእነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም፤ ለርግማንም አይወልዱም።
24“እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፤ ገናም ሲናገሩ እነሆ፥ አለሁ እላቸዋለሁ። 25ያንጊዜ ተኵላና በግ በአንድነት ይሰማራሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፤ አያጠፉምም፥” ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 65: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ