ትንቢተ ኢሳይያስ 64
64
1ሰማይን ብትከፍት ከአንተ የተነሣ ተራሮች ይንቀጠቀጣሉ፤ ይቀልጣሉም። 2አደሮ ማር በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ እንዲሁ ጠላቶችህን እሳት ትበላቸዋለች፤ ስምህም በእነርሱ ላይ ይታወቃል፤ አሕዛብም በፊትህ ይደነግጣሉ። 3የክብርህንም ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ ተራሮች በፊትህ ተንቀጠቀጡ። 4ከጥንት ጀምሮ ይቅርታህን ለሚጠባበቁ ምሕረትን ከምታደርግላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክ አላየንም፤ አልሰማንምም። 5በቸርነትህ የሚታገሡ መንገድህንም የሚያስቡ ይገናኙሃል፤ እነሆ፥ አንተ ተቈጣህ፤ እኛም ኀጢአት ሠራን፤ ስለዚህም ተሳሳትን። 6ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፤ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ በኀጢአታችን ምክንያት እንደ ቅጠል ረግፈናል፤ እንዲሁም ነፋስ ጠራርጎ ወስዶናል። 7ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ መልሰሃል፤ ለኀጢአታችንም አሳልፈህ ሰጥተኸናል።
8አሁን ግን፥ ጌታ ሆይ፥ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን፤#“አንተም ሠሪያችን ነህ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። አንተም ሠሪያችን ነህ፤ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። 9አቤቱ፥ እጅግ አትቈጣ፤ ለዘለዓለምም ኀጢአታችንን አታስብ፤ አሁንም እባክህ፥ ወደ እኛ ተመልከት፤ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን። 10የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል፤ ጽዮን ምድረ በዳ ኢየሩሳሌምም ውድማ ሆናለች። 11አባቶቻችን ያከበሩት ክብራችን ቤተ መቅደስህ በእሳት ተቃጥሎአል፤ ያማረውም ስፍራችን ፈርሶአል። 12አቤቱ፥ በዚህ ነገር ሁሉ ታገሥኸን፤ ዝም አልኸን፤ እጅግም አዋረድኸን።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 64: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ