ትንቢተ ኢሳይያስ 63
63
የአሕዛብ ድል መሆን
1ከኤዶምያስ፥ ከባሶራ የሚመጣ፥ ልብሱም የቀላ፥ የሚመካ ኀይለኛ፥ አለባበሱም ያማረ፥ ይህ ማን ነው? ስለ ጽድቅ የምከራከር፥ ስለ ማዳንም የምፈርድ እኔ ነኝ። 2ቀሚስህ ስለ ምን ቀላ? ልብስህስ በወይን መጭመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ስለ ምን መሰለ? 3መጭመቂያውን ብቻዬን ረግጫለሁ፤ ከአሕዛብም አንድ ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፤ በቍጣዬም ረገጥኋቸው፤ በመዓቴም ወደ መሬት ጣልጥህዋቸው፤ ደማቸውንም በምድር ላይ አፈሰስሁ፤ ልብሴም ሁሉ በደም ታለለ።#“ልብሴም ሁሉ በደም ታለለ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 4የምበቀልበት ቀን ደርሶባቸዋልና፥ የምቤዥበትም ዐመት ደርሶአልና። 5የሚረዳም እንደሌለ አየሁ፤ የሚያግዝም እንደሌለ ዐወቅሁ፤ ስለዚህ በገዛ ክንዴ አድናቸዋለሁ፤ ቍጣዬም ወደቀችባቸው። 6በመቅሠፍቴ ረገጥኋቸው፤ ደማቸውንም ወደ ምድር አፈሰስሁት።
የእግዚአብሔር ቸርነት ለእስራኤል
7በስጦታው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና ዐሰብሁ፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ወገኖች እውነተኛ ፈራጅ ነው፤ እንደ ቸርነቱና እንደ ጽድቁ ብዛትም ይቅርታውን ያመጣልናል። 8እርሱም፥ “ሕዝቤ ልጆች አይደሉምን? ካልከዱኝስ ከመከራቸው ሁሉ አድናቸዋለሁ” አለ። 9በመልእክተኛም አይደለም፤ በመልአክም አይደለም፤ እርሱ ራሱ ያድናቸዋል እንጂ። እርሱ ይወዳቸዋልና፥ ይራራላቸዋልምና እርሱ ተቤዣቸው፤ ተቀበላቸውም፤ በዘመናቸውም ሁሉ ለዘለዓለም አከበራቸው።
10እነርሱ ግን ዐመፁበት፤ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፤ እርሱም ተዋጋቸው። 11እርሱም እንዲህ ብሎ የቀደመውን ዘመን ዐሰበ፥ “በበጎቹ እረኛ እጅ ከግብፅ በወጡ ጊዜ መልአኬን በፊታቸው ላክሁ። 12በሙሴም ቀኝ እጅ ውኃውን ከፈልሁ፤” ውኃውም ተከፍሎ በፊቱ ጸና፤ የዘለዓለም ስምንም አደረገለት።#ምዕ. 63 ቍ. 11 እና 12 በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. ልዩ ነው። 13ፈረስ በምድረ በዳ እንደሚያልፍ፥ በቀላይ ውስጥ አሳለፋቸው፥ እነርሱም አልደከሙም። 14ወደ ሸለቆ እንደሚወርዱ ከብቶች፥ እንዲሁ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዕረፍት አመጣቸው፤ እንዲሁም ለራስህ የከበረ ስምን ታደርግ ዘንድ ሕዝብህን መራህ።
ምሕረትንና ርዳታን ለመግኘት የቀረበ ጸሎት
15ከሰማይ ተመለስ፤ ከቅድስናህና ከክብርህ ማደሪያም ተመልከት፤ ቅንአትህና ኀይልህስ ወዴት ነው? የቸርነትህና የይቅርታህ ብዛት ወዴት ነው? ቸል ብለሃልና። 16አንተ አባታችን ነህ፤ አብርሃም ግን አላወቀንም፤ እስራኤልም አልተገነዘበንም፤ ነገር ግን አንተ አባታችን አድነን፤ ስምህም ለዘለዓለም በእኛ ላይ#ዕብ. “ታዳጊያችን” ይላል። ነው። 17አቤቱ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ፤ 18በተቀደሰው ተራራህ ከርስትህ ጥቂት ክፍል እናገኝ ዘንድ።#ዕብ. “የተቀደሰው ሕዝብህ መቅደስህን ጥቂት ጊዜ ወረሱአት፥ ጠላቶቻችንም ረግጠውታል” ይላል። 19ከጥንት እንዳልገዛኸን ስምህም በእኛ ላይ እንዳልተጠራ ሆነናልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 63: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ