ትንቢተ ኢሳይያስ 62
62
1ጽድቄ#ዕብ. “ጽድቅዋ” ይላል። እንደ ብርሃን፥ ማዳኔም እንደሚበራ ፋና እስኪወጣ ድረስ ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም። 2አሕዛብ ጽድቅሽን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔርም አፍ#“አፍ” የሚለው በዕብ. ብቻ። በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ። 3በእግዚአብሔር እጅ ያማረ አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ። 4ከእንግዲህ ወዲህ፥ “የተተወች” አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፥ “ውድማ” አትባልም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ብሎታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፥ “ደስታዬ የሚኖርባት” ትባያለሽ፤ ምድርሽም፥ “ባል ያገባች” ትባላለች። 5ጐልማሳም ከድንግሊቱ ጋር እንደሚኖር፥ እንዲሁ ልጆችሽ ከአንቺ ጋር ይኖራሉ፤ ሙሽራም በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፥ እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል።
6ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ጠባቂዎችሽን በቅጥርሽ ላይ ቀንና ሌሊት አቁሜአለሁ፤ እግዚአብሔርን የሚያስቡ ከቶ ዝም አይሉም፤ 7ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና፥ በምድርም ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ ዝም አትበሉ። 8እግዚአብሔር፥ “ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፤” ብሎ በጌትነቱና በክንዱ ኀይል ምሎአል። 9ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፤ ያከማቹትንም ወይን በመቅደሴ አደባባይ ላይ ይጠጡታል።
10ሂዱና በበሬ ውስጥ ግቡ፤ ለሕዝቤም መንገድን ጥረጉ፤ ድንጋዮቹንም ከጎዳናው አስወግዱ፤ ለአሕዛብም አላማ ያዙ። 11እነሆ፥ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል፥ “ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ መድኀኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ አለ በሉአት።” 12እግዚአብሔር፥ “የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፥ “የተተወች ያይደለች የተወደደች ቅድስት ከተማ” ትባያለሽ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 62: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ