ትንቢተ ኢሳይያስ 65
65
1 #
ሮሜ 10፥20። ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ፦ “አለሁኝ፥ አለሁኝ” አልኩት። 2#ሮሜ 10፥21።መልካም ባልሆነው መንገድ፥ አሳባቸውን እየተከተሉ፥ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ። 3ይህ ሕዝብ ዘወትር በፊቴ ቁጣን ይቀሰቅሳሉ፥ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ፥ በጡብም ላይ የሚያጥኑ፥ 4በመቃብርም መካከል የሚቀመጡ፥ ምሽቱንም በስውርም ስፍራ የሚያሳልፉ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። ማሰሮዎቻቸው በረከሰ ነገር የተሞሉ ናቸው። 5እነርሱም፦ “ለራስህ ቁም፥ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ” ይላሉ፤ እነዚህ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት፥ በአፍንጫዬ ስር የምታልፍ ጢስ ናቸው። 6እነሆ፥ በፊቴ እንዲህ ተጽፎአል፦ “ዝም አልልም፤ ነገር ግን እንደ ሥራው እሰጠዋለሁ፤ የእጃቸውንም እከፍላቸዋለሁ። 7በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ ሰደቡኝ፥ ስለዚህ አስቀድመው ለሠሩት ሥራቸውን የእጃቸውን እሰጣቸዋለሁ።” 8ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወይን በዘለላው በተገኘች ጊዜ፥ “በረከት በእርሷ ላይ አለና አታጥፉት” እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፋ ስለ አገልጋዮቼ እንዲሁ አደርጋለሁ። 9ከያዕቆብም ዘርን ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤ እኔም የመረጥኳቸው ይወርሷታል፥ አገልጋዬቼም በዚያ ይኖራሉ። 10#ኢያ. 7፥24-26።ለፈለገኝ ሕዝቤ ሳሮን የበጎች ማሰማርያ፥ የአኮር ሸለቆ የላሞች መመሰግያ ይሆናል። 11እናንተን ጌታን የተዋችሁትን ግን፥ ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን፥ ዕጣ ፋንታ ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን፥ ዕድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን የቀዳችሁትን፥ 12እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ፥ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፥ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራኋችሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝም፤ በተናገርኩም ጊዜ አልሰማችሁኝም። 13ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ አገልጋዮቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤ 14እነሆ፥ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፥ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ። 15ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ አገልጋዮቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል። 16እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፥ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ ምክንያቱም የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአል፥ ከዓይኔም ተሰውሮአል።
የከበረው አዲስ ፍጥረት
17 #
ኢሳ. 66፥22፤ 2ጴጥ. 3፥13፤ ራእ. 21፥1። እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁ፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ትውስታቸውም አይኖርም። 18ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘለዓለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና። 19#ራእ. 21፥4።እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም። 20ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጎልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ የመቶ ዓመት ሳይሆነው የሚሞት እንደተረገመ ኃጢአተኛ ይታያል። 21ቤትም ይሠራሉ ይኖሩበታል፤ ወይንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። 22ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል። 23እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም። 24እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፥ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ። 25#ኢሳ. 11፥6-9።ተኩላና ጠቦት በአንድነት ይሠማራሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፤ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ጉዳት አያደርሱም፥ አያጠፉምም፥ ይላል ጌታ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 65: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ