ትንቢተ ኢሳይያስ 64

64
1ምነው ሰማያትን ቀደህ ብትወርድ! ምነው ተራሮችም ቢናወጡ! 2እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ እንዲገለጥ፥ አሕዛብም በፊትህ እንዲንቀጠቀጡ፤ 3ያልተጠባበቅነውን የክብርህን ሥራ ባደረግህ ጊዜ፥ አንተ ወረድህ፥ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ። 4#1ቆሮ. 2፥9።ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ማንም አልሰሙም፥ የትኛውም ጆሮ አልተቀበለውም፥ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላችው ከአንተ አምላካችን በቀር ሌላ ማንም አላየውም። 5ጽድቅን የሚያደርገውን፥ በመንገዶችህም የሚያስቡህን ትገናኛቸዋለህ። እኛ ኃጢአት ሠራን፤ እነሆ፥ አንተ ተቈጥተህ ነበር፤ ፊትህን ስለሰወርክብን እኛ ተሳሳትን። 6ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። 7ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም ሊይዝ የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ ሰውረሃል፥ በኃጢአታችንም አጥፍተኸናል። 8አሁን ግን፥ አቤቱ ጌታ፥ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ጭቃ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፥ እኛም ሁላችን የእጅህ ሥራ ነን። 9አቤቱ ጌታ፥ እጅግ አትቈጣ፥ ለዘለዓለምም ኃጢአትን አታስብ፤ እነሆ፥ እባክህ፥ ተመልከት፥ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነን። 10የተቀደሱ ከተሞችህ ምድረ በዳ ሆነዋል፤ ጽዮን ምድረ በዳ፥ ኢየሩሳሌምም የተተወች ሆናለች። 11አባቶቻችን አንተን ያመሰገኑበት የተቀደሰና የተዋበ ቤታችን በእሳት ተቃጥሎአል፤ ያማረውም ስፍራችን ሁሉ ፈራርሷል። 12አቤቱ ጌታ፥ በውኑ በዚህ ነገር ትታገሣለህን? ዝምስ ትላለህን? አጥብቀህስ ታስጨንቀናለህን?

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ