ኢሳይያስ 29:1-10
ኢሳይያስ 29:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዳዊት የሰፈረብሽ ከተማ፣ አርኤል፣ አርኤል ወዮልሽ! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሪ፣ ዐውደ ዓመትሽም ይቀጥል። ነገር ግን አርኤልን እከብባለሁ፤ ታለቅሳለች፤ ዋይ ዋይ ትላለች፤ ለእኔም እንደ መሠዊያ ስፍራ ትሆንልኛለች። በዙሪያሽ እሰፍራለሁ፤ በቅጥር እከብብሻለሁ፤ የከበባ ዐምባም ሠርቼ አስጨንቅሻለሁ። ወደ ታች ትወርጃለሽ፤ ከምድርም በታች ትናገሪያለሽ፤ ንግግርሽ ከትቢያ እየተጕተመተመ ይወጣል፤ ድምፅሽ እንደ መናፍስት ድምፅ ከመሬት ወደ ላይ ይመጣል፤ ንግግርሽ ከትቢያ ያንሾካሹካል። ነገር ግን ብዙ ጠላቶችሽ እንደ ትቢያ ብናኝ፣ የጨካኞች መንጋ በነፋስ እንደሚነዳ ገለባ ይሆናሉ። ድንገት ሳይታሰብም፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በነጐድጓድ፣ በምድር መናወጥና በታላቅ ድምፅ፣ በዐውሎ ነፋስና በኀይለኛ ሞገድ፣ ፈጽሞ በሚባላም የእሳት ነበልባል ይመጣል። አርኤልን የሚወጋ የአሕዛብ ሁሉ መንጋ፣ በእርሷና በምሽጓ ላይ አደጋ የሚጥልና የሚከብባት፣ እንደ ሕልም በሌሊትም እንደሚታይ ራእይ ይሆናል። የተራበ ሰው በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ፣ ነገር ግን ሲነቃ ራቡ እንዳልለቀቀው፣ የጠማውም ሰው በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ፣ ነገር ግን ሲነቃ እንደ ዛለና ጥማቱም እንዳልተወው፣ የጽዮንን ተራራ የሚወጋ፣ የአሕዛብ መንጋ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል። ነኹልሉ ተደነቁም፤ ተጨፈኑ፤ እስከ ወዲያኛውም ታውራችሁ ቅሩ፤ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ፤ በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ። እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ጥሎባችኋል፤ ዐይኖቻችሁን፣ ነቢያትን ጨፍኖባችኋል፤ ራሶቻችሁን፣ ባለራእዮችን ሸፍኖባችኋል።
ኢሳይያስ 29:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ ለአርኤል ወዮላት! የዓመቱን አዝመራ ሰብስቡ፤ ከሞዓብ ጋር ትበላላችሁና። አርኤልንም አስጨንቃለሁ፤ ይህችም ኀይል፥ ይህችም ብዕል የእኔ ትሆናለች፥ እንደ ዳዊትም እከብሻለሁ፤ በቅጥርም አጥርሻለሁ፤ አንባም በላይሽ አቆማለሁ። ነገርሽም በምድር ውስጥ ይሰጥማል፤ ቃልሽም ከምድር በታች እንደሚናገር ይሆናል፤ ትደክሚያለሽ፤ ቃልሽም በምድር ውስጥ ዝቅ ይላል። ነገር ግን የኃጥአን ብልጽግና እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጠላቶችሽም ብዛት ነፋስ እንደሚያመጣው ገለባ ይሆናል። ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅ ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ ኢየሩሳሌምንም የሚወጉ፥ በእርሻዋም ላይ የሚሰበሰቡ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብልጽግና እንደሚያልም ሰው ሕልም ነው። ሰዎች ተርበው ሌሊት በሕልማቸው ይበላሉ፤ ይጠጣሉም፤ በተነሡ ጊዜ ግን ሕልማቸው ከንቱ ነው። የተጠማ ሰውም እንደሚጠጣ ያልማል፤ በነቃም ጊዜ እንደ ተጠማ ነው፤ ነፍሱም በከንቱ ትመኛለች። ደብረ ጽዮንን የሚዋጉ የአሕዛብ ብልጽግናም እንደዚሁ ነው። ደከሙ፤ ደነገጡም፤ ሰከሩም፤ በወይን አይይደለም፤ በጠጅም አይደለም። እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን አፍስሶባቸዋል፤ ዐይኖቻቸውን፥ የነቢያትንም ዐይን፥ የተሰወረውንም የሚያዩ የአለቆቻቸውን ዐይን ጨፍኖባቸዋል።
ኢሳይያስ 29:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ ለአርኤል ወዮላት! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ፥ በዓላትም ይመለሱ። አርኤልንም አስጨንቃለሁ፥ ልቅሶና ዋይታም ይሆንባታል፥ እንደ አርኤልም ትሆንልኛለች። በዙሪያሽም እሰፍራለሁ፥ በቅጥርም ከብቤ አስጨንቅሻለሁ፥ አምባም በላይሽ አቆማለሁ። ትዋረጅማለሽ፥ በመሬትም ላይ ሆነሽ ትናገሪያለሽ፥ ቃልሽም ዝቅ ብሎ ከአፈር ይወጣል፥ ድምጽሽም ከመሬት እንደሚወጣ እንደ መንፍስት ጠሪ ድምፅ ይሆናል፥ ቃልሽም ከአፈር ወጥቶ ይጮኸል። ነገር ግን የጠላቶችሽ ብዛት እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጨካኞችም ብዛት እንደሚያልፍ ገለባ ይሆናል። ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅም ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ እርስዋንና ምሽግዋንም የሚወጉ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደ ሕልምና እንደ ሌሊት ራእይ ይሆናል። ተርቦም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፥ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይበላል፥ ነገር ግን ይነቃል ሰውነቱም ባዶ ነው፥ ተጠምቶም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፥ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይጠጣል፥ ነገር ግን ይነቃል፥ እነሆም፥ ይዝላል ሰውነቱም አምሮት አለው፥ እንዲሁም የጽዮንን ተራራ የሚወጉ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት ይሆናል። ተደነቁ ደንግጡም፥ ተጨፈኑም ዕውሮችም ሁኑ፥ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ፥ በሚያሰክር መጠጥ እይሁን እንጂ ተንገደገዱ። እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል ዓይኖቻችሁን ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።
ኢሳይያስ 29:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አሪኤል ተብላ ለምትጠራው ዳዊት ለሠፈረባት ለኢየሩሳሌም ከተማ ወዮላት! ዓመቶች ይደጋገሙ፤ በዓላትም በየዓመቱ ይከበሩ። ከዚያ በኋላ ግን እኔ እግዚአብሔር “የእግዚአብሔር መሠዊያ” ተብላ የምትጠራውን የእስራኤል ከተማ አስጨንቃለሁ፤ እዚያም ሐዘንና የለቅሶ ዋይታ ይሆናል፤ ከተማይቱም በደም እንደ ተሸፈነ መሠዊያ ትሆናለች። በዙሪያውም ግንብና ምሽግ ሠርቼ አስጨንቃታለሁ። በየመጠበቂያው ላይ ጠባቂዎችን አቆማለሁ። በቅጥርም መወጣጫ አሠራለሁ። ካለችበት ከጥልቁ ጒድጓድ ትናገራለች፤ ከታች ከትቢያ ውስጥ ንግግርዋ ይመጣል፤ ድምፅዋም እንደ ምትሐት ከምድረ በዳ ይወጣል፤ ከአዋራ ውስጥም ዝቅ ያለ ድምፅዋ ይሰማል። ኢየሩሳሌም ሆይ! በአንቺ ላይ በጠላትነት የሚነሡ የጠላት ሠራዊት ሁሉ እንደ ትቢያ በነው ይጠፋሉ፤ እጅግ የሚያስፈሩ ሠራዊቶቻቸውም ሳይታሰቡ በድንገት በነፋስ እንደሚወሰድ ገለባ ይሆናሉ። የሠራዊት ጌታ አምላክ ነጐድጓድን፥ የመሬት መናወጥን፥ ታላቅ ድምፅን፥ ዐውሎ ነፋስን፥ ሞገድንና የሚባላ የእሳት ነበልባልን በጠላቶችሽ ላይ በመላክ አንቺን ይታደግሻል። የእግዚአብሔር መሠዊያ የሆነችውን ከተማ ለማጥቃት የሚመጡ የመንግሥታት ሠራዊቶች ሁሉ ከነጦር መሣሪያዎቻቸው ይደመሰሳሉ፤ እንደ ሕልም ወይም በእንቅልፍ ልብ እንደሚታሰብ ነገር የተረሱ ይሆናሉ። በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል የተሰበሰቡ መንግሥታት ሁሉ በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ ጠዋት በነቃ ጊዜ ምንም ያልቀመሰ ረኃብተኛ መሆኑንና እንዲሁም በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ ጧት በነቃ ጊዜ ጒሮሮው በውሃ ጥም ደርቆ እንደሚያገኘው ሰው ይሆናሉ። እንደ ደነቈራችሁና እንደ ታወራችሁ ቅሩ! ምንም ወይን ጠጅ ሳትጠጡ የሰከራችሁ ሁኑ! ምንም ዐይነት የሚያሰክር መጠጥ ሳትቀምሱ ተንገዳገዱ! እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ስለ ጣለባችሁ እናንተ ነቢያት ዐይኖቻችሁን ጨፍናችኋል፤ እናንተም ባለ ራእዮች አእምሮአችሁን ዘግታችኋል።
ኢሳይያስ 29:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳዊት የሰፈረብሽ ከተማ አርኤል፥ አንቺ አርኤል ወዮልሽ! ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ፥ በዓላትም ይመላለሱ። ግን አርኤልንም አስጨንቃለሁ፥ ልቅሶና ዋይታም ይሆንባታል፤ እሷም እንደ አርኤል ትሆንልኛለች። በዙሪያሽም እሰፍራለሁ፥ በቅጥርም ከብቤ አስጨንቅሻለሁ፥ የጥበቃ አምባም በላይሽ አቆማለሁ። ትዋረጃለሽ፥ መሬት ላይ ተደፍተሽ ትናገሪያለሽ፥ ቃልሽም በዝግታ ከአፈር ይወጣል፤ ድምጽሽም ከመሬት እንደሚወጣ እንደ መናፍስት ድምፅ ይሆናል፥ ንግግርሽም ከአፈር በሹክሹክታ ይወጣል። ነገር ግን የጠላቶችሽ ብዛት እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጨካኞችም ብዛት እንደሚያልፍ ገለባ ይሆናል። ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅም ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ እርሷንና ምሽግዋንም የሚወጉ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደ ሕልምና፥ እንደ ሌሊት ራእይ ይሆናል። ተርቦም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይበላል፥ ነገር ግን ይነቃል ሰውነቱም ባዶ ነው፤ ተጠምቶም እንደሚያልም ሰው ይሆናል፤ በሕልሙም፥ እነሆ፥ ይጠጣል፥ ነገር ግን ይነቃል፥ እነሆም፥ ይዝላል ሰውነቱም እንደተጠማ አለ፤ የጽዮንን ተራራም የሚወጉ የአሕዛብ ሁሉ ብዛት እንደዚሁ ይሆናል። ተደነቁ ደንግጡም፤ ጨፍኑ ታወሩም! ስክሩም፥ በወይን ጠጅ አይደለም፤ ተንገዳገዱ፥ በመጠጥ አይደለም። ጌታ የሚደብት የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል፤ ዐይኖቻችሁን፥ ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል፤ ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።