አሪኤል ተብላ ለምትጠራው ዳዊት ለሠፈረባት ለኢየሩሳሌም ከተማ ወዮላት! ዓመቶች ይደጋገሙ፤ በዓላትም በየዓመቱ ይከበሩ። ከዚያ በኋላ ግን እኔ እግዚአብሔር “የእግዚአብሔር መሠዊያ” ተብላ የምትጠራውን የእስራኤል ከተማ አስጨንቃለሁ፤ እዚያም ሐዘንና የለቅሶ ዋይታ ይሆናል፤ ከተማይቱም በደም እንደ ተሸፈነ መሠዊያ ትሆናለች። በዙሪያውም ግንብና ምሽግ ሠርቼ አስጨንቃታለሁ። በየመጠበቂያው ላይ ጠባቂዎችን አቆማለሁ። በቅጥርም መወጣጫ አሠራለሁ። ካለችበት ከጥልቁ ጒድጓድ ትናገራለች፤ ከታች ከትቢያ ውስጥ ንግግርዋ ይመጣል፤ ድምፅዋም እንደ ምትሐት ከምድረ በዳ ይወጣል፤ ከአዋራ ውስጥም ዝቅ ያለ ድምፅዋ ይሰማል። ኢየሩሳሌም ሆይ! በአንቺ ላይ በጠላትነት የሚነሡ የጠላት ሠራዊት ሁሉ እንደ ትቢያ በነው ይጠፋሉ፤ እጅግ የሚያስፈሩ ሠራዊቶቻቸውም ሳይታሰቡ በድንገት በነፋስ እንደሚወሰድ ገለባ ይሆናሉ። የሠራዊት ጌታ አምላክ ነጐድጓድን፥ የመሬት መናወጥን፥ ታላቅ ድምፅን፥ ዐውሎ ነፋስን፥ ሞገድንና የሚባላ የእሳት ነበልባልን በጠላቶችሽ ላይ በመላክ አንቺን ይታደግሻል። የእግዚአብሔር መሠዊያ የሆነችውን ከተማ ለማጥቃት የሚመጡ የመንግሥታት ሠራዊቶች ሁሉ ከነጦር መሣሪያዎቻቸው ይደመሰሳሉ፤ እንደ ሕልም ወይም በእንቅልፍ ልብ እንደሚታሰብ ነገር የተረሱ ይሆናሉ። በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል የተሰበሰቡ መንግሥታት ሁሉ በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ ጠዋት በነቃ ጊዜ ምንም ያልቀመሰ ረኃብተኛ መሆኑንና እንዲሁም በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ ጧት በነቃ ጊዜ ጒሮሮው በውሃ ጥም ደርቆ እንደሚያገኘው ሰው ይሆናሉ። እንደ ደነቈራችሁና እንደ ታወራችሁ ቅሩ! ምንም ወይን ጠጅ ሳትጠጡ የሰከራችሁ ሁኑ! ምንም ዐይነት የሚያሰክር መጠጥ ሳትቀምሱ ተንገዳገዱ! እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ስለ ጣለባችሁ እናንተ ነቢያት ዐይኖቻችሁን ጨፍናችኋል፤ እናንተም ባለ ራእዮች አእምሮአችሁን ዘግታችኋል።
ትንቢተ ኢሳይያስ 29 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 29:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos