ትንቢተ ኢሳይያስ 29
29
ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ መከበብ
1ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ ለአርኤል ወዮላት! የዓመቱን አዝመራ ሰብስቡ፤ ከሞዓብ ጋር ትበላላችሁና።#ዕብ. “ዓመት በዓመት ላይ ጨምሩ ፤ በዓላትም ይመለሱ” ይላል። 2አርኤልንም#“አርኤል” የኢየሩሳሌም የመጀመሪያ ስምዋ ነው። አስጨንቃለሁ፤ ይህችም ኀይል፥ ይህችም ብዕል የእኔ ትሆናለች፥#ዕብ. “ልቅሶና ዋይታም ይሆንበታል እንደ አርኤልም ትሆንልኛለች” ይላል። 3እንደ ዳዊትም እከብሻለሁ፤ በቅጥርም አጥርሻለሁ፤ አንባም በላይሽ አቆማለሁ። 4ነገርሽም በምድር ውስጥ ይሰጥማል፤ ቃልሽም ከምድር በታች እንደሚናገር ይሆናል፤ ትደክሚያለሽ፤ ቃልሽም በምድር ውስጥ ዝቅ ይላል።
5ነገር ግን የኃጥአን ብልጽግና እንደ ደቀቀ ትቢያ፥ የጠላቶችሽም ብዛት ነፋስ እንደሚያመጣው ገለባ ይሆናል። 6ድንገትም ፈጥኖ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በነጐድጓድ፥ በምድርም መናወጥ፥ በታላቅ ድምፅ፥ በዐውሎ ነፋስም፥ በወጨፎም፥ በምትበላም በእሳት ነበልባል ይጐበኛታል። 7በአርኤልም ላይ የሚዋጉ፥ ኢየሩሳሌምንም የሚወጉ፥ በእርሻዋም ላይ የሚሰበሰቡ የሚያስጨንቋትም፥ የአሕዛብ ሁሉ ብልጽግና#ዕብ. “ብዛት” ይላል። እንደሚያልም ሰው ሕልም ነው። 8ሰዎች ተርበው ሌሊት በሕልማቸው ይበላሉ፤ ይጠጣሉም፤ በተነሡ ጊዜ ግን ሕልማቸው ከንቱ ነው። የተጠማ ሰውም እንደሚጠጣ ያልማል፤ በነቃም ጊዜ እንደ ተጠማ ነው፤ ነፍሱም በከንቱ ትመኛለች። ደብረ ጽዮንን የሚዋጉ የአሕዛብ ብልጽግናም እንደዚሁ ነው።
9ደከሙ፤ ደነገጡም፤ ሰከሩም፤ በወይን አይይደለም፤ በጠጅም አይደለም።#ዕብ. “ተጨፈኑም ዕውሮችም ሆኑ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ሰከሩ በሚያሰክር ጠጅ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ” ይላል። 10እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስን አፍስሶባቸዋል፤ ዐይኖቻቸውን፥ የነቢያትንም ዐይን፥ የተሰወረውንም የሚያዩ የአለቆቻቸውን ዐይን ጨፍኖባቸዋል። 11ይህም ሁሉ ነገር እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባቸዋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ፥ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፥ “ታትሟልና ማንበብ አልችልም” ይላቸዋል፤ 12ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ፥ “ይህን አንብብ” ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ፥ “ማንበብ አላውቅም” ይላቸዋል።
13ጌታም አለ፥ “ይህ ሕዝብ በከንፈሮቹ ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በከንቱ ያመልኩኛል፤ ሰው ሠራሽ ትምህርትም ያስተምራሉ፤ 14ስለዚህ፥ እነሆ፥ ይህ ሕዝብ በድጋሚ እንዲፈልስ አደርጋለሁ፤ አፈልሳቸዋለሁም፤ የጥበበኞችንም ጥበብ አጠፋለሁ፤ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እሰውራለሁ።”
15ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ ወዮላቸው! ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው፥ “ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል?” ለሚሉ ወዮላቸው! 16ይህ የእናንተ ጠማምነት ነው፤ እንደ ሸክላ ሠሪ ጭቃ የምትቈጠሩ አይደላችሁምን? በውኑ ሥራ ሠሪውን፥ “አልሠራኸኝም” ይለዋልን? ወይስ የተደረገ አድራጊውን፥ “በማስተዋል አላሳመርኸኝም” ይለዋልን?
17ሊባኖስ እንደ ፍሬያማ እርሻ ሊለወጥ፥ ፍሬያማውም እርሻ እንደ ዱር ሊቈጠር ጥቂት ዘመን የቀረ አይይደለምን? 18በዚያም ቀን ደንቆሮች የመጽሐፍን ቃል ይሰማሉ፤ በጨለማና በጭጋግ ውስጥም የዕውሮች ዐይኖች ያያሉ። 19ነዳያን ደስታቸውን በእግዚአብሔር ያበዛሉ፤ በሰዎች መካከል ተስፋ የሌላቸውም ሐሤትን በእስራኤል ቅዱስ#“... በእስራኤል ቅዱስ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ያደርጋሉ። 20ኃጥእ ሰው አልቆአልና፥ ትዕቢተኛውም ጠፍቶአልና፥ በክፋት የበደሉም ሁሉ ይነቀላሉና፤ 21እነዚህም ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፥ በበርም ለሚገሥጸው አሽክላ የሚያኖሩ፥ ጻድቁንም በከንቱ ነገር የሚያስቱ ናቸው።
22ስለዚህ እግዚአብሔር ከአብርሃም ስለ ለየው ስለ ያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፥ “ያዕቆብ አሁን አታፍርም፤ ፊትህም አሁን አይለወጥም። 23ነገር ግን ልጆቻቸው የእጄን ሥራ ባዩ ጊዜ ስለ እኔ ስሜን ይቀድሳሉ፤ የያዕቆብንም ቅዱስ ይቀድሳሉ፤ የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ። 24በመንፈስም የሳቱ ማስተዋልን ያውቃሉ፤ የሚያጕረመርሙም መታዘዝን ይማራሉ፤ ዲዳ አንደበትም ሰላም መናገርን ይማራል።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 29: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ