ትንቢተ ኢሳይያስ 28
28
ስለ ኤፍሬም የተነገረ ማስጠንቀቂያ
1ለኤፍሬም ምንደኞች ትዕቢት አክሊል፥ ያለ ወይን ጠጅ ለሰከሩ፥ በወፍራም ተራራ ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብር ጌጥ አበባ ወዮ! 2እነሆ፥ ኀያል ብርቱ የሆነ የእግዚአብሔር መቅሠፍት በኀይል እንደሚወርድ የበረዶ ወጨፎ፥ እንደሚያጠፋም ዐውሎ ነፋስ፥ እንደሚያጥለቀልቅም እንደ ብዙ ውኃ ፈሳሽ በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላል። 3የኤፍሬም ምንደኞች ትዕቢት አክሊል በእጅና በእግር ይረገጣል፤ 4በረዥም ተራራ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ተስፋ አበባ አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ ሰውም ባያት ጊዜ በእጁ ሳይቀበላት ይበላት ዘንድ ይፈጥናል። 5በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለተረፉት ሕዝቡ የክብር የተጐነጐነ ዘውድና የተስፋ አክሊል ይሆናል። 6ለፍርድና ከጥፋት ለሚያድናቸው ኀይል በፍርድ መንፈስ ይቀራሉ።#ዕብ. “በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ፥ ሰልፉን ወደ በር ለሚመልሱም ኀይል ይሆናል” ይላል።
7እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፤ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ አላዋቆች ይሆናሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፤ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፤ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይበድላሉ፤ ይህም የዐይን ምትሐት ነው፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “መርገም ይህችን ምክር ትበላለች ምክራቸውም ስለ መጐምጀት ነውና ይህች ናት” ይላል። በፍርድ ይሰናከላሉ። 8ማዕዱም ሁሉ ትፋትንና ርኵሰትን ተሞልቶአል፤ ንጹሕ ስፍራ እንኳን የለም።
9ክፉን ለማን ተናገርን? ወሬን ለማን አወራን?#ዕብ. “ዕውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል” ይላል። ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን? 10ሕማምን በሕማም ላይ፥ ተስፋንም በተስፋ ላይ ተቀበሉ፤#ዕብ. “ትእዛዝ በትእዛዝ ትእዛዝ በትዕዛዝ ፤ ሥርዐት በሥርዐት ሥርዐት በሥርዐት ...” ይላል። ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። 11በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ 12እርሱም፥ “ይህችም ለደከመ ዕረፍት ናት፤ ይህችም መቅሠፍት ናት፤” አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። 13ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፥ እንዲሰበሩም፥ ተጠምደውም እንዲቸገሩ፥ የግዚአብሔርም ቃሉ በሕማም ላይ ሕማም፥ በተስፋ ላይ ተስፋ፥#ዕብ. “ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትዕዛዝ ፤ ሥርዐት በሥርዐት ሥርዐት በሥርዐት ...” ይላል። ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል።
የጽዮን የማዕዘን ድንጋይ
14ስለዚህ የተጨነቃችሁ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ አለቆች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 15እናንተም “ከሲኦል ጋር ተማምለናል፤ ከሞትም ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፤ ሐሰትንም መሸሸጊያን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና፥ ዐውሎ ነፋስም ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም” ትላላችሁና፥ 16ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ ዋጋው ብዙ የሆነውን፥ የተመረጠውን፥ የከበረውንና መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ አኖራለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም። 17ፍርዴን ለተስፋ ይቅርታዬንም ለትክክለኛ ሚዛን አደርጋለሁ፤ በከንቱና በሐሰት የሚታመኑ ከዐውሎ ነፋስ አያመልጡም። 18ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፤ ከኢኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚያልፍ ዐውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ ይረግጣችኋል፤ ትደክማላችሁም። 19ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ ማለዳ ማለዳ በቀን ያልፋል፤ በሌሊት ክፉ ተስፋ ይሆናል፤ እናንተ ያዘናችሁ፥ መስማትን ተማሩ።” 20መዋጋትን አንችልም፤ እናንተንም ለመሰብሰብ ደካሞች ነን።#“ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጐናጸፊያው ጠባብ ነው” 21እግዚአብሔርም በኃጥኣን ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፤ በገባዖን ሸለቆም ይኖራል፤ ሥራውን ማለት መራራ ሥራውን በቍጣ ይሠራል፤ ቍጣውም ድንቅን ያደርጋል፤ መርዙም ልዩ ነው። 22አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚያደርገውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራታችሁ እንዳይጸናባችሁ እናንተ ደስ አይበላችሁ።
23አድምጡ፤ ድምፄንም ስሙ፤ ልብ አድርጉ፤ ንግግሬንም ስሙ። 24በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ምድሩን ከማረሱ አስቀድሞ ዘርን ይዘራልን? ጓሉንስ ይከሰክሳልን? 25እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቂት ጥቍሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ዳግመኛም ስንዴውን፥ ገብሱንም፥ አጃውንም በየስፍራው የሚዘራ አይደለምን? 26ምድርም የእግዚአብሔርን ፍርድ ተምራ ደስ ይላታል።#ዕብ. “ይህንም ብልሃት አምላኩ ያስታውቀዋል ያስተምረውማል” ይላል። 27ጥቍሩን አዝሙድ በተሳለች ማሄጃ አያሄድም፤ የሰረገላም መንኰራኵር በከሙን ላይ አይዞርም፤ ነገር ግን ጥቍሩን አዝሙድ በሽመል፥ ከሙኑንም በበትር ይወቃል። 28#ዕብ. “የእንጀራ እህል ይደቅቃልን? ለዘለዓለም አያኬደውም የሰረገላውን መንኰራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቅቀውም” ይላል።እኔ ለዘለዓለም በእናንተ ላይ አልቈጣም፤ የምሕረቴም ድምፅ አያጠፋችሁም። 29ይህም ደግሞ ድንቅ ምክርን ከሚመክር በግብሩም ገናና ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል። እናንተ ግን ከንቱ መጽናናትን ታበዙ ዘንድ ትሻላችሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 28: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ