ትንቢተ ኢሳይያስ 27
27
ስለ እስራኤል መዳን
1በዚያም ቀን እግዚአብሔር በፈጣኑ እባብ ደራጎን ላይ፥ በክፉውም እባብ ደራጎን ላይ ልዩ፥ ታላቅና ብርቱ ሰይፍን ያመጣል። በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድለዋል።
2በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት። 3እኔ የጸናች ከተማ ነኝ፤ አንድዋን ከተማ ይወጋሉ። በከንቱ አጠጣኋት፤ በሌሊት ትጠመዳለች፤ በቀንም ግድግዳዋ ይወድቃል፤ የሚያነሣትም የለም።#ዕብ. “እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ ፤ ሁልጊዜ አጠጣዋለሁ ፤ ማንም እንዳይጐዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ” ይላል። 4ስለ ጠቡ በእሳት አቃጥለው ዘንድ ቀርቃሃና ሣርን ማን በሰጠኝ! አሁንም እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ ዛሬ አደረገ፤ እነርሱ ተቃጥለዋልና።#ዕብ. “አልቈጣም እሾህና ኩርንችት በእኔ ላይ ምነው በሰልፍ በነበሩ፥ በእነርሱ ላይ ተራምጄ በአንድነት ባቃጠልኋቸው ነበር!” ይላል። 5በውስጧ የሚኖሩ ይጮሃሉ፤ ከእርሱ ጋር ሰላምን እናድርግ፤ ከእርሱ ጋር ሰላምን እናድርግ። 6በሚመጣው ዘመን የያዕቆብ ልጆች ሥር ይሰድዳሉ፤ እስራኤልም ያብባል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ።
7በውኑ የመቱትን እንደ መታ እንዲሁ እርሱን መታውን? ወይስ እነርሱ እንደ ተገደሉበት መገደል እርሱ ተገድሎአልን? 8በጠብና በንቀት ይሰዳቸዋል፤ በቍጣና በክፉ መንፈስ ትገሥጻቸው ዘንድ ትጀምራለህን?#ዕብ. “ነዳቸው፥ ሰደዳቸው፥ ቀሠፋቸው፥ የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን በጠንካራ ዐውሎ አስወገዳቸው” ይላል። 9ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፤ ይህም ኀጢአትን የማስወገድ ፍሬ ሁሉ ነው። 10በዚያም የተሰማራው መንጋ እንደ ተተወ መንጋ ይሆናል፤ ምድሩም ለብዙ ዘመን መሰማሪያ ይሆናል፤ በዚያም መንጋው ይሰማራል፤ ያርፋልም። 11ዘግይቶ ይደርቃል፤ በውስጡም ልምላሜ ሁሉ አይገኝም፤ ከቲኣሳ የምትመጡ ሴቶች፥ ኑና ለሕዝቤ አልቅሱ፤ የማያስተውል ሕዝብ ነውና፤ ስለዚህ ፈጣሪው አይራራለትም፤ ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም።
12በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ፈሳሽ ጀምሮ እስከ ግብፅ ወንዝ ድረስ ዐጥር ያጥራል፤ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ።
13በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦርም የጠፉ፥ በግብፅ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፤ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 27: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ