ትንቢተ ኢሳይያስ 26
26
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ድልን እንደሚሰጥ
1በዚያም ቀን ይህን ቅኔ በይሁዳ ምድር ይዘምራሉ፤ እነሆም፥ የጸናችና የምታድን፥ ቅጥርንና ምሽግንም የምታደርግ ከተማ አለችን። 2ፍትሕን የሚጠብቅና ጽድቅን የሚያደርግ ሕዝብ ይገባ ዘንድ በሮችን ክፈቱ። 3በአንተ ላይ ታምናለችና በአንተ የምትደገፍ ነፍስን ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ። 4ጌታ እግዚአብሔር የዘለዓለም አንባ ነውና ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታመኑ። 5በከፍታ የሚኖሩትን ሰዎች ዝቅ ታደርጋለህ፤ የተመሸጉትንም ከተሞች ትጥላለህ፤ እስከ ምድርም ድረስ ታወርዳቸዋለህ።#ዕብ. “እስከ አፈር ድረስም ታፈርሳቸዋለህ” ይላል። 6የየዋሃንና የትሑታን እግሮች ይረግጡአቸዋል።
7የጻድቃን መንገድ የቀና ትሆናለች፤ የቅኖችም መንገድ ትጠረጋለች። 8የእግዚአብሔር መንገድ የቀና ነው፤ በቅዱስ ስሙም ታመን፤ ነፍሳችን የተመኘችውንም አገኘን። 9አቤቱ፥ አምላኬ ሆይ፥ ትእዛዝህ በምድር ላይ ብርሃን ነውና ነፍሴ በሌሊት ወደ አንተ ትገሠግሣለች። በምድር የምትኖሩም ጽድቅ መሥራትን ተማሩ። 10በምድር ጽድቅን የማይማርና መልካምን የማያደርግ ኃጥእ አልቆአልና፥ የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ኀጢአተኛን ያስወግዱታል።
11አቤቱ፥ ከፍ ያለች ክንድህን አላወቁም፤ ካወቁ ግን ያፍራሉ። አላዋቆች ሰዎችን ቅንአት ያዛቸው፤ አሁንም እሳት ጠላቶችን ትበላለች። 12አቤቱ፥ አምላካችን ሁሉን ሰጥተኸናልና ሰላምን ስጠን። 13አቤቱ፥ አምላካችን ሆይ፥ አንተ ግዛን፤ ከአንተ በቀር ሌላ አናውቅምና፤ ስምህንም እንጠራለን።
14ነገር ግን ሙታን ሕይወትን አያዩአትም፤ ባለ መድኀኒቶችም አያስነሡም፤ ስለዚህም አንተ አምጥተሃቸዋል፤ አጥፍተሃቸውማል፤ ወንዶቻቸውንም#ግእዙ “ትዕቢቶሙ” ይላል። ሁሉ አስወግደሃል። 15አቤቱ፥ ክፋትን ጨምርባቸው፤ ለምድር ክቡራን ክፋትን ጨምርባቸው።
16አቤቱ፥ በመከራዬ ጊዜ አሰብኹህ፤ በጥቂት መከራም ገሠጽኸኝ። 17የፀነሰች ሴት ለመውለድ ስትቀርብ እንደምትጨነቅና በምጥ እንደምትጮህ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ በፊትህ ለወዳጅህ ሆነናል። 18አንተን በመፍራት አቤቱ፥ እኛ ፀንሰናል፤ ምጥም ይዞናል፤ በምድርም የማዳንህን መንፈስ ወለድን፤ በዓለምም የሚኖሩ ይወድቃሉ። 19ሙታን ይነሣሉ፤ በመቃብር ያሉም ይድናሉ። በምድርም የሚኖሩ ደስ ይላቸዋል፤ ከአንተ የሚገኝ ጠል መድኀኒታቸው ነውና፤ የኃጥኣንንም ምድር ታጠፋለህ።
20ሕዝቤ ሆይ፥ ና፤ ወደ ቤትህም ግባ፤ ደጅህን በኋላህ ዝጋ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ። 21እነሆ፥ እግዚአብሔር በምድር በሚኖሩት ላይ ከመቅደሱ መቅሠፍቱን ያመጣል፤ ምድርም ደምዋን ትገልጣለች፤ ሙታኖችዋንም ከእንግዲህ ወዲህ አትከድንም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 26: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ