ዕብራውያን 7:1-24
ዕብራውያን 7:1-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህ መልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበር፤ እርሱም አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ አግኝቶት ባረከው፤ አብርሃምም ከሁሉ ነገር ዐሥራትን አውጥቶ ሰጠው። በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ኋላም ደግሞ “የሳሌም ንጉሥ” ማለትም “የሰላም ንጉሥ ማለት” ነው። አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ የለውም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ልጅ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። እስኪ እርሱ የቱን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ አስቡ፤ ርእሰ አበው የሆነው አብርሃም እንኳ ካገኘው ምርኮ ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው! ክህነት የተሰጣቸው የሌዊ ልጆች ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም፣ ከሕዝቡ ማለት ከገዛ ወንድሞቻቸው ዐሥራት እንዲቀበሉ ሕጉ ያዝዛል። ይህ ግን ትውልዱ ከሌዊ ወገን አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከአብርሃም ዐሥራት ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተቀበለውንም ባረከው። ትንሹ በትልቁ እንደሚባረክ ጥርጥር የለውም። በአንድ በኩል ዐሥራት የሚቀበሉት ሟች ሰዎች ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት ይቀበላል። እንዲያውም ዐሥራት የሚቀበለው ሌዊ፣ ራሱ በአብርሃም በኩል ዐሥራት ከፍሏል ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም መልከ ጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ፣ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ነበር። ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ? የክህነት ለውጥ ካለ ሕጉም ሊለወጥ ግድ ነውና። ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን ቢነሣ ግን እኛ የተናገርነው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤ እርሱ ካህን የሆነው በማይጠፋ የሕይወት ኀይል መሠረት እንጂ፣ እንደ ትውልዱ የሕግ ሥርዐት አይደለም፤ እንዲህ ተብሎ ተመስክሮለታል፤ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።” የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሯል፤ ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቷል። ይህ ያለ መሐላ አልሆነም። ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤ “ጌታ ማለ፤ አሳቡንም አይለውጥም፤ ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ” ከዚህ መሐላ የተነሣ፣ ኢየሱስ ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኗል። በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት ስለ ከለከላቸው፣ የቀድሞዎቹ ካህናት ቍጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘላለም የሚኖር በመሆኑ፣ ክህነቱ የማይሻር ነው።
ዕብራውያን 7:1-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሳሌም ንጉሥ፥ የልዑል እግዚአብሔርም ካህን የሆነ፥ ይህ መልከ ጼዴቅ፥ አብርሃም ነገሥታትን ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው። አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው፤ መጀመሪያ የስሙ ትርጓሜ የጽድቅ ንጉሥ ነበር፤ በኋላም የሳሌም ንጉሥ ተባለ፤ የሰላም ንጉሥ ማለት ነው። አባት የለውም፤ እናትም የለችውም፤ ትውልዱም አይታወቅም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፥ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ክህነቱ የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል። የአባቶች አለቃ አብርሃም ከምርኮው ሁሉ የሚሻለውን ዐሥራት የሰጠውን የዚህን ካህን ክብር ታያላችሁን? ከሌዊ ልጆችም፥ ክህነትን የሚቀበሉት ከሕዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ ከእነርሱ ዐሥራትን በሕግ እንዲያስወጡ ትእዛዝ አላቸው። ወገናቸው ላይደለ ለእርሱ ግን አብርሃም ዐሥራትን ሰጠው፤ እርሱም ተስፋ ያለው አብርሃምን ባረከው። ነገር ግን ታላቁ ታናሹን እንደሚባርከው ያለ ጥርጥር ይታወቃል። በዚህስ የሚሞት ሰው ዐሥራትን ይቀበላል፤ በወዲያው ግን ሕያው እንደ ሆነ መጽሐፍ የሚመሰክርለት እርሱ ይቀበላል። እንደ ተነገረም ዐሥራትን የሚቀበል ሌዊ ስንኳን በአብርሃም በኩል ዐሥራትን ሰጠ። መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ በአብርሃም ወገብ ነበርና። እንግዲህ ሕዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ወደ ፊት ስለምን ያስፈልጋል? ክህነታቸው ታልፍ ዘንድ አላትና፤ ክህነታቸው ካለፈችም ኦሪታቸው ታልፋለች። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ ወጣ የተገለጠ ነውና፤ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳን ስለ ክህነት አልተናገረም። ይልቁንም ይህ እጅግ ያስረዳል፤ በመልከ ጼዴቅ ክህነት አምሳል ሌላ ካህን ይነሣል ብሎአልና። ይኸውም በማያልፍ ሕይወት ኀይል እንጂ ለሥጋና ለደም በተሠራ ሕግ አይደለም። “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን አንተ ነህ” ብሎ ይመሰክራልና። ስለዚህም የምትደክም፥ የማትጠቅምም ስለ ሆነች የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች። ኦሪት ምንም ግዳጅ አልፈጸመችምና፤ ነገር ግን በእርስዋ ፋንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእርስዋ የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እርሱ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ያለ መሐላ የተሾሙ ካህናት አሉና። በመሐላ የሾመውን ግን፥ “እግዚአብሔር ማለ፥ አይጸጸትምም፤ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን ነህ” አለው። ኢየሱስ ይህን ያህል በምትበልጥና ከፍ ባለች ሹመት ተሾመ። ለእነዚያስ ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው፤ ሞት ይሽራቸው፥ እንዲኖሩም አያሰናበታቸውም ነበርና። እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና።
ዕብራውያን 7:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ አስራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። የአባቶች አለቃ አብርሃም ከዘረፋው የሚሻለውን አስራት የሰጠው ይህ ሰው እንዴት ትልቅ እንደ ነበረ እስኪ ተመልከቱ። ከሌዊ ልጆችም ክህነትን የሚቀበሉት ከህዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ፥ ከእነርሱ አሥራትን በሕግ እንዲያስወጡ ትእዛዝ አላቸው፤ ትውልዱ ከእነርሱ የማይቍኦጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል። ትንሹንም በታላቁ እንዲባርክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው። በዚህስ የሚሞቱ ሰዎች አሥራትን ያስወጣሉ፥ በዚያ ግን የሚያስወጣ በሕይወት እንዲኖር የተመሰከረለት እርሱ ነው። ይህንም ለማለት ሲፈቀድ፥ አሥራትን የሚያስወጣ ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል፤ መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበረና። እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቍኦጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ የግድ ነውና። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም፤ ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና፥ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳ ስለ ክህነት አልተናገረም። በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ ሳይሆን ሌላ ካህን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ቢነሳ፥ ይህ እጅግ አብልጦ የሚገለጥ ነው። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ይመሰክራልና። ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ፦ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥ እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤
ዕብራውያን 7:1-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መልከጼዴቅ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበር፤ ይህ መልከጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን አሸንፎ ሲመለስ በመንገድ ተገናኝቶ ባረከው። አብርሃምም ከያዘው ነገር ሁሉ ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው፤ የመልከ ጼዴቅ የስሙ ትርጓሜ አንደኛው “የጽድቅ ንጉሥ” ሌላው “የሳሌም ንጉሥ” ወይም “የሰላም ንጉሥ” ማለት ነው። መልከጼዴቅ በጽሑፍ የታወቀ አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ የለውም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፥ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ይህ መልከጼዴቅ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ምሳሌ በመሆን ለዘለዓለም ካህን ሆኖ ይኖራል። ይህ ሰው እንዴት ታላቅ እንደ ሆነ ተመልከቱ፤ የነገድ አባት የሆነው አብርሃም እንኳ በምርኮ ካገኘው ነገር ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው። እነዚያ በክህነት ሥራ ላይ የሚመደቡት የሌዊ ዘሮች ከሕዝቡ ከአብርሃም ዘር ማለትም ከወንድሞቻቸው ዐሥራት እንዲቀበሉ በሕግ ታዞላቸዋል፤ ያ መልከጼዴቅ የሌዋውያን ዘር ባይሆንም እንኳ ከአብርሃም ዐሥራትን ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተሰጠውን አብርሃምንም ባረከው። ታናሹ ከታላቁ ቡራኬን እንደሚቀበል ጥርጥር የለውም። በአንድ በኩል ዐሥራት የሚቀበሉት ሟች የሆኑት ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ዐሥራት የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት መልከጼዴቅ ነው። እንግዲህ መልከጼዴቅ አብርሃምን በተገናኘው ጊዜ ሌዊ ከአባቱ ከአብርሃም ገና ስላልተወለደ ዐሥራትን መቀበል የሚገባው ሌዊ ራሱ በአብርሃም አማካይነት ዐሥራትን ከፍሎአል ማለት ነው። እንግዲህ ለሕዝቡ ሕግ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ነው፤ በዚህ በሌዋውያን ክህነት ፍጹምነት ቢገኝ ኖሮ የአሮን የክህነት ሹመት ሳይሆን የመልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣት ባላስፈለገም ነበር፤ የክህነት ሐረጉ ሲለወጥ ሕጉም አብሮ መለወጥ አለበት። ይህ ሁሉ የተነገረለት ካህን ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር የይሁዳን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። ይህ ነገር በጣም ግልጥ ሆኖ የሚገኘው እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ነው፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው በመሆኑ ነው እንጂ ከዘር በመጣ ሥርዓትና ሕግ አይደለም። “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም ስለ ሆነ ተሽሮአል በሙሴ ሕግ ምንም ነገር ፍጹም ሊሆን አልቻለም፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ ተሰጥቶናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ እግዚአብሔር መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ ኢየሱስ ግን ካህን የሆነው በእግዚአብሔር መሐላ ነው፤ ይህም፦ “እግዚአብሔር ‘አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሎአል፤ አይለውጥም” ተብሎ በተነገረለት መሠረት ነው። በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት አንድ ካህን ሳይለወጥ በሥራው ላይ ለዘለዓለም መኖር ስለማይችል የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘለዓለም የሚኖር በመሆኑ ክህነቱ የማይለወጥ ነው።
ዕብራውያን 7:1-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የሳሌም ንጉሥ፥ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ፥ ይህ መልከጼዴቅ፥ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ አግኝቶት ባረከው፤ ለእርሱም አብርሃም ከሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው፥፥ የስሙ ትርጓሜ በመጀመሪያ፥ የጽድቅ ንጉሥ ነው፤ ከዚያ ደግሞ፥ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት የትውልድም ሐረግም የሉትም፤ ለዘመኑም መጀመሪያ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። ይህ ሰው እንዴት ታላቅ እንደሆነ እስቲ ተመልከቱ! የአባቶች አለቃ የሆነው አብርሃም እንኳ በምርኮ ካገኘው ነገር አሥራት አውጥቶ ሰጠው። ከሌዊ ልጆችም፥ ክህነትን የሚቀበሉት ከሕዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነዚያ ክህነትን የሚቀበሉት የሌዊ ልጆች ከሕዝቡ ማለትም ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ፥ አሥራትን እንዲቀበሉ በሕግ ታዞላቸዋል። ይህ ሰው ምንም ትውልዱ ከእነርሱ ባይቆጠርም እንኳ ከአብርሃም አሥራትን ተቀብሏል፤ የተስፋ ቃል የተሰጠውን አብርሃምንም ባርኮአል። ታናሹ በታላቁ እንደሚባረክ ምንም ጥርጥር የሌለውም። በዚህ በኩል የሚሞቱ ሰዎች አሥራትን ይቀበላሉ፤ በዚያ በኩል የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት እርሱ ነው። በመሆኑም አሥራትን የሚቀበለው ሌዊ ራሱ እንኳን፥ በአብርሃም በኩል አሥራትን ሰጥቶአል፥ ማለት ያስችላል፤ ምክንያቱም መልከጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበር። እንግዲህ በሌዊ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ከሆነ፥ ሕዝቡ በዚያ ላይ የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና፤ ወደ ፊት እንደ አሮን ሹመት የሚቆጠር ሳይሆን፥ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ስለምን ያስፈልጋል? ምክንያቱም ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ ግድ ይላልና ነው። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ ወጣ የታወቀ ነው፤ ከዚያ ነገድ ጋር በተገናኘ ስለ ካህናት ሙሴ ምንም አልተናገረም። ይህ ይበልጥ እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ግልጽ ይሆናል፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ አይደለም። ስለ እርሱ “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። ስለዚህም ደካማና የማትጠቅም ስለ ሆነች፥ የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች፤ ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፤ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ተዋውቀናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና፤ “ጌታ ሐሳቡን አይቀይርም ‘አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ፤’ ብሎ ምሏል፥፥” በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት በክህነት ሥራ ላይ ለመቆየት ስላልቻሉ፥ የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤