የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ዕብራውያን 7:1-24

ወደ ዕብራውያን 7:1-24 መቅካእኤ

የሳሌም ንጉሥ፥ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ፥ ይህ መልከጼዴቅ፥ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ አግኝቶት ባረከው፤ ለእርሱም አብርሃም ከሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው፥፥ የስሙ ትርጓሜ በመጀመሪያ፥ የጽድቅ ንጉሥ ነው፤ ከዚያ ደግሞ፥ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። አባትና እናት የትውልድም ሐረግም የሉትም፤ ለዘመኑም መጀመሪያ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። ይህ ሰው እንዴት ታላቅ እንደሆነ እስቲ ተመልከቱ! የአባቶች አለቃ የሆነው አብርሃም እንኳ በምርኮ ካገኘው ነገር አሥራት አውጥቶ ሰጠው። ከሌዊ ልጆችም፥ ክህነትን የሚቀበሉት ከሕዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነዚያ ክህነትን የሚቀበሉት የሌዊ ልጆች ከሕዝቡ ማለትም ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ፥ አሥራትን እንዲቀበሉ በሕግ ታዞላቸዋል። ይህ ሰው ምንም ትውልዱ ከእነርሱ ባይቆጠርም እንኳ ከአብርሃም አሥራትን ተቀብሏል፤ የተስፋ ቃል የተሰጠውን አብርሃምንም ባርኮአል። ታናሹ በታላቁ እንደሚባረክ ምንም ጥርጥር የሌለውም። በዚህ በኩል የሚሞቱ ሰዎች አሥራትን ይቀበላሉ፤ በዚያ በኩል የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት እርሱ ነው። በመሆኑም አሥራትን የሚቀበለው ሌዊ ራሱ እንኳን፥ በአብርሃም በኩል አሥራትን ሰጥቶአል፥ ማለት ያስችላል፤ ምክንያቱም መልከጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበር። እንግዲህ በሌዊ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ከሆነ፥ ሕዝቡ በዚያ ላይ የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና፤ ወደ ፊት እንደ አሮን ሹመት የሚቆጠር ሳይሆን፥ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ስለምን ያስፈልጋል? ምክንያቱም ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ ግድ ይላልና ነው። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ ወጣ የታወቀ ነው፤ ከዚያ ነገድ ጋር በተገናኘ ስለ ካህናት ሙሴ ምንም አልተናገረም። ይህ ይበልጥ እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ግልጽ ይሆናል፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ አይደለም። ስለ እርሱ “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። ስለዚህም ደካማና የማትጠቅም ስለ ሆነች፥ የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች፤ ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፤ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ተዋውቀናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና፤ “ጌታ ሐሳቡን አይቀይርም ‘አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ፤’ ብሎ ምሏል፥፥” በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት በክህነት ሥራ ላይ ለመቆየት ስላልቻሉ፥ የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤