የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዕብራውያን 7:1-24

ዕብራውያን 7:1-24 NASV

ይህ መልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበር፤ እርሱም አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ አግኝቶት ባረከው፤ አብርሃምም ከሁሉ ነገር ዐሥራትን አውጥቶ ሰጠው። በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ኋላም ደግሞ “የሳሌም ንጉሥ” ማለትም “የሰላም ንጉሥ ማለት” ነው። አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ የለውም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ልጅ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። እስኪ እርሱ የቱን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ አስቡ፤ ርእሰ አበው የሆነው አብርሃም እንኳ ካገኘው ምርኮ ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው! ክህነት የተሰጣቸው የሌዊ ልጆች ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም፣ ከሕዝቡ ማለት ከገዛ ወንድሞቻቸው ዐሥራት እንዲቀበሉ ሕጉ ያዝዛል። ይህ ግን ትውልዱ ከሌዊ ወገን አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከአብርሃም ዐሥራት ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተቀበለውንም ባረከው። ትንሹ በትልቁ እንደሚባረክ ጥርጥር የለውም። በአንድ በኩል ዐሥራት የሚቀበሉት ሟች ሰዎች ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት ይቀበላል። እንዲያውም ዐሥራት የሚቀበለው ሌዊ፣ ራሱ በአብርሃም በኩል ዐሥራት ከፍሏል ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም መልከ ጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ፣ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ነበር። ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ? የክህነት ለውጥ ካለ ሕጉም ሊለወጥ ግድ ነውና። ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን ቢነሣ ግን እኛ የተናገርነው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤ እርሱ ካህን የሆነው በማይጠፋ የሕይወት ኀይል መሠረት እንጂ፣ እንደ ትውልዱ የሕግ ሥርዐት አይደለም፤ እንዲህ ተብሎ ተመስክሮለታል፤ “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።” የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሯል፤ ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቷል። ይህ ያለ መሐላ አልሆነም። ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤ “ጌታ ማለ፤ አሳቡንም አይለውጥም፤ ‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ” ከዚህ መሐላ የተነሣ፣ ኢየሱስ ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኗል። በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት ስለ ከለከላቸው፣ የቀድሞዎቹ ካህናት ቍጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘላለም የሚኖር በመሆኑ፣ ክህነቱ የማይሻር ነው።