የሳሌም ንጉሥ፥ የልዑል እግዚአብሔርም ካህን የሆነ፥ ይህ መልከ ጼዴቅ፥ አብርሃም ነገሥታትን ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው። አብርሃምም ከገንዘቡ ሁሉ ከዐሥር አንድ ሰጠው፤ መጀመሪያ የስሙ ትርጓሜ የጽድቅ ንጉሥ ነበር፤ በኋላም የሳሌም ንጉሥ ተባለ፤ የሰላም ንጉሥ ማለት ነው። አባት የለውም፤ እናትም የለችውም፤ ትውልዱም አይታወቅም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፥ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ክህነቱ የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል። የአባቶች አለቃ አብርሃም ከምርኮው ሁሉ የሚሻለውን ዐሥራት የሰጠውን የዚህን ካህን ክብር ታያላችሁን? ከሌዊ ልጆችም፥ ክህነትን የሚቀበሉት ከሕዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ ከእነርሱ ዐሥራትን በሕግ እንዲያስወጡ ትእዛዝ አላቸው። ወገናቸው ላይደለ ለእርሱ ግን አብርሃም ዐሥራትን ሰጠው፤ እርሱም ተስፋ ያለው አብርሃምን ባረከው። ነገር ግን ታላቁ ታናሹን እንደሚባርከው ያለ ጥርጥር ይታወቃል። በዚህስ የሚሞት ሰው ዐሥራትን ይቀበላል፤ በወዲያው ግን ሕያው እንደ ሆነ መጽሐፍ የሚመሰክርለት እርሱ ይቀበላል። እንደ ተነገረም ዐሥራትን የሚቀበል ሌዊ ስንኳን በአብርሃም በኩል ዐሥራትን ሰጠ። መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ በአብርሃም ወገብ ነበርና። እንግዲህ ሕዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሣ ወደ ፊት ስለምን ያስፈልጋል? ክህነታቸው ታልፍ ዘንድ አላትና፤ ክህነታቸው ካለፈችም ኦሪታቸው ታልፋለች። ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ ወጣ የተገለጠ ነውና፤ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳን ስለ ክህነት አልተናገረም። ይልቁንም ይህ እጅግ ያስረዳል፤ በመልከ ጼዴቅ ክህነት አምሳል ሌላ ካህን ይነሣል ብሎአልና። ይኸውም በማያልፍ ሕይወት ኀይል እንጂ ለሥጋና ለደም በተሠራ ሕግ አይደለም። “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን አንተ ነህ” ብሎ ይመሰክራልና። ስለዚህም የምትደክም፥ የማትጠቅምም ስለ ሆነች የቀደመችው ትእዛዝ ተሽራለች። ኦሪት ምንም ግዳጅ አልፈጸመችምና፤ ነገር ግን በእርስዋ ፋንታ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ከእርስዋ የሚሻል ተስፋ ገብቶአል። እርሱ ያለ መሐላ አልሆነም፤ ያለ መሐላ የተሾሙ ካህናት አሉና። በመሐላ የሾመውን ግን፥ “እግዚአብሔር ማለ፥ አይጸጸትምም፤ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዘለዓለም ካህን ነህ” አለው። ኢየሱስ ይህን ያህል በምትበልጥና ከፍ ባለች ሹመት ተሾመ። ለእነዚያስ ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው፤ ሞት ይሽራቸው፥ እንዲኖሩም አያሰናበታቸውም ነበርና። እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና።
ወደ ዕብራውያን 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ዕብራውያን 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ዕብራውያን 7:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች