የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 7:1-24

ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት 7:1-24 አማ05

መልከጼዴቅ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበር፤ ይህ መልከጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን አሸንፎ ሲመለስ በመንገድ ተገናኝቶ ባረከው። አብርሃምም ከያዘው ነገር ሁሉ ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው፤ የመልከ ጼዴቅ የስሙ ትርጓሜ አንደኛው “የጽድቅ ንጉሥ” ሌላው “የሳሌም ንጉሥ” ወይም “የሰላም ንጉሥ” ማለት ነው። መልከጼዴቅ በጽሑፍ የታወቀ አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ የለውም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፥ ለሕይወቱም መጨረሻ የለውም፤ ይህ መልከጼዴቅ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ምሳሌ በመሆን ለዘለዓለም ካህን ሆኖ ይኖራል። ይህ ሰው እንዴት ታላቅ እንደ ሆነ ተመልከቱ፤ የነገድ አባት የሆነው አብርሃም እንኳ በምርኮ ካገኘው ነገር ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው። እነዚያ በክህነት ሥራ ላይ የሚመደቡት የሌዊ ዘሮች ከሕዝቡ ከአብርሃም ዘር ማለትም ከወንድሞቻቸው ዐሥራት እንዲቀበሉ በሕግ ታዞላቸዋል፤ ያ መልከጼዴቅ የሌዋውያን ዘር ባይሆንም እንኳ ከአብርሃም ዐሥራትን ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተሰጠውን አብርሃምንም ባረከው። ታናሹ ከታላቁ ቡራኬን እንደሚቀበል ጥርጥር የለውም። በአንድ በኩል ዐሥራት የሚቀበሉት ሟች የሆኑት ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ዐሥራት የሚቀበለው ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት መልከጼዴቅ ነው። እንግዲህ መልከጼዴቅ አብርሃምን በተገናኘው ጊዜ ሌዊ ከአባቱ ከአብርሃም ገና ስላልተወለደ ዐሥራትን መቀበል የሚገባው ሌዊ ራሱ በአብርሃም አማካይነት ዐሥራትን ከፍሎአል ማለት ነው። እንግዲህ ለሕዝቡ ሕግ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ነው፤ በዚህ በሌዋውያን ክህነት ፍጹምነት ቢገኝ ኖሮ የአሮን የክህነት ሹመት ሳይሆን የመልከ ጼዴቅ የክህነት ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣት ባላስፈለገም ነበር፤ የክህነት ሐረጉ ሲለወጥ ሕጉም አብሮ መለወጥ አለበት። ይህ ሁሉ የተነገረለት ካህን ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚህ ነገድ ማንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ያገለገለ የለም። ጌታችን ከይሁዳ ነገድ መሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር የይሁዳን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። ይህ ነገር በጣም ግልጥ ሆኖ የሚገኘው እንደ መልከጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን በሚነሣበት ጊዜ ነው፤ እሱ የክህነት ሹመትን የተቀበለው ለሕይወቱ ፍጻሜ የሌለው በመሆኑ ነው እንጂ ከዘር በመጣ ሥርዓትና ሕግ አይደለም። “እንደ መልከጼዴቅ የክህነት ሹመት አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ” ተብሎ ተመስክሮለታል። የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም ስለ ሆነ ተሽሮአል በሙሴ ሕግ ምንም ነገር ፍጹም ሊሆን አልቻለም፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ ተሰጥቶናል። ከዚህም በቀር ይህ ክህነት ያለ እግዚአብሔር መሐላ አልሆነም፤ እነዚያ ከዚህ በፊት ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ ኢየሱስ ግን ካህን የሆነው በእግዚአብሔር መሐላ ነው፤ ይህም፦ “እግዚአብሔር ‘አንተ ለዘለዓለም ካህን ነህ’ ብሎ ምሎአል፤ አይለውጥም” ተብሎ በተነገረለት መሠረት ነው። በዚህ መሐላ ምክንያት ኢየሱስ ለተሻለው ቃል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። በሞት ምክንያት አንድ ካህን ሳይለወጥ በሥራው ላይ ለዘለዓለም መኖር ስለማይችል የቀድሞዎቹ ካህናት ቊጥራቸው ብዙ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ለዘለዓለም የሚኖር በመሆኑ ክህነቱ የማይለወጥ ነው።