ዘፍጥረት 39:1-10
ዘፍጥረት 39:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፣ ግብጻዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። አሳዳሪውም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወለት ባየ ጊዜ፣ ዮሴፍ በርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ፣ እግዚአብሔር የግብጻዊውን ቤት ባረከ፤ የእግዚአብሔርም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በቀር፣ ማንኛውንም ጕዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ እያደርም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለች፤ አፍ አውጥታም፣ “ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጕተውም፣ አልሰማትም፤ ከርሷ ጋራ መተኛት ይቅርና ዐብሯትም መሆን አልፈቀደም።
ዘፍጥረት 39:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዮሴፍ ግን ወደ ግብፅ ወረደ፤ የፈርዖን ጃንደረባ የመጋቢዎቹም አለቃ የሚሆን የግብፅ ሰው ጲጥፋራ ወደ ግብፅ ከአወረዱት ከይስማኤላውያን እጅ ገዛው። እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ተሾመ። ጌታውም እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንዳለ፥ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ። ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ፤ እርሱንም ደስ ያሰኘው ነበር፤ በቤቱም ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው። እንዲህም ሆነ፤ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኋላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት በዮሴፍ ምክንያት ባረከው። የእግዚአብሔርም በረከት በቤቱም፥ በእርሻውም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ። ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ በእጁ አስረከበው፤ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም። ዮሴፍም መልኩ ያማረ፥ ፊቱም እጅግ የተዋበ ነበር። ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይንዋን ጣለችበት፤ “ከእኔም ጋር ተኛ” አለችው። እርሱም እንቢ አለ፤ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት፥ “እነሆ፥ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ሁሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፤ በቤቱ ያለውንም ምንም የሚያውቀው የለም፤ በዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለሆንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኀጢአትን እሠራለሁ?” ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ፥ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም።
ዘፍጥረት 39:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዮሴፍ ግን ወደ ግብፅ ወረደ፤ የፈርዖን ጃንደረባ የዘበኞቹም አለቃ የሚሆን የግብፅ ሰው ዺጥፋራ ወደ ግብፅ ካወረዱት ከእስማኤላዉያን እጅ ገዛው። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ፥ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ነበረ። ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ እርሱንም ያገለግለው ነበር በቤቱም ላይ ሾመው ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው። እንዲህም ሆነ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኍላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት ስለ ዮሴፍ ባረከው የእግዚአብሔር በረከት በውጪም በግቢም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ። ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ አስረከበ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም። የዮሴርም ፊቱ መልከ መልካምን ውብ ነበረ። ከዚህም በኍላ እንዲህ ሆነ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች፦ ከእኔም ጋር ተኛ አለችው። እርሱም እንቢ አለ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት፦ እነሆ ጌታዬ በቤት ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የስም ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤ ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፋ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ? ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም።
ዘፍጥረት 39:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስማኤላውያን ነጋዴዎች ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት፤ እዚያም ከግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ባለሥልጣኖች አንዱ ለሆነው ለጶጢፋር ሸጡት፤ ጶጢፋር የተባለው ግብጻዊ፥ የፈርዖን የዘበኞች አለቃ ነበር። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ ስለዚህም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ሲኖር ሁሉ ነገር ተቃናለት። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንደ ነበረና ሥራውንም ሁሉ እንዳቃናለት ባየ ጊዜ፥ ጶጢፋር ዮሴፍን ወደደው፤ የቅርብ አገልጋዩም አደረገው፤ በቤቱ ላይ አዛዥነትን፥ በንብረቱም ሁሉ ላይ ኀላፊነትን ሰጠው። ይህም ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር በዮሴፍ ምክንያት የግብጻዊውን ሰው ቤት ንብረትና በውጪም በእርሻ ያለውን ሀብት ሁሉ ባረከለት። ስለዚህ ጶጢፋር ያለውን ንብረት ሁሉ በዮሴፍ ቊጥጥር ሥር አደረገ፤ ጶጢፋር ከሚመገበው ምግብ በስተቀር የሚያውቀው ምንም ነገር አልነበረም። ዮሴፍ ቁመናው የተስተካከለ መልከ መልካም ሰው ነበር። ከጊዜ በኋላ የጌታው ሚስት ዮሴፍን ተመልክታ ስለ አፈቀረችው፥ “ና ከእኔ ጋር አብረን እንተኛ” አለችው። እርሱ ግን ይህን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፤ ስለዚህም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሁሉንም ነገር በእኔ ኀላፊነት ሥር ስላደረገ፥ በቤቱ ውስጥ ስላለው ንብረት ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፤ ያለውን ንብረት ሁሉ እንዳስተዳድርለት በዐደራ ለእኔ ሰጥቶኛል። ጌታዬ በዚህ ቤት ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት የለውም፤ ከአንቺ በቀር በእኔ ቊጥጥር ሥር ያላደረገው ምንም ነገር የለም፤ ይኸውም ሚስቱ ስለ ሆንሽ ነው፤ ታዲያ ይህን አስከፊ ኃጢአት በመፈጸም እግዚአብሔርን እንዴት አሳዝናለሁ?” እርስዋም ይህንኑ ጉዳይ በየቀኑ ትነግረው ነበር፤ ዮሴፍ ግን አብሮአት መተኛት ወይም በአጠገቧ ለመገኘት አልፈለገም።
ዘፍጥረት 39:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምንት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፥ ግብፃዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው። ጌታ ከዮሴፍ ጋር ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብፃዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። አሳዳሪውም ጌታ ከእርሱ ጋር እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወነለት ባየ ጊዜ፥ ዮሴፍ በእርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ጌታ የግብፃዊውን ቤት ባረከ፥ የጌታም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በስተቀር፥ ማናቸውንም ጉዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ እያደርም የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፥ “አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፥ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፥ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጉተውም፥ አልሰማትም፤ ከእርሷ ጋር መተኛቱ ይቅርና አብሯትም መሆን አልፈቀደም።