እስማኤላውያን ነጋዴዎች ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት፤ እዚያም ከግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ባለሥልጣኖች አንዱ ለሆነው ለጶጢፋር ሸጡት፤ ጶጢፋር የተባለው ግብጻዊ፥ የፈርዖን የዘበኞች አለቃ ነበር። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ ስለዚህም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ሲኖር ሁሉ ነገር ተቃናለት። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንደ ነበረና ሥራውንም ሁሉ እንዳቃናለት ባየ ጊዜ፥ ጶጢፋር ዮሴፍን ወደደው፤ የቅርብ አገልጋዩም አደረገው፤ በቤቱ ላይ አዛዥነትን፥ በንብረቱም ሁሉ ላይ ኀላፊነትን ሰጠው። ይህም ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር በዮሴፍ ምክንያት የግብጻዊውን ሰው ቤት ንብረትና በውጪም በእርሻ ያለውን ሀብት ሁሉ ባረከለት። ስለዚህ ጶጢፋር ያለውን ንብረት ሁሉ በዮሴፍ ቊጥጥር ሥር አደረገ፤ ጶጢፋር ከሚመገበው ምግብ በስተቀር የሚያውቀው ምንም ነገር አልነበረም። ዮሴፍ ቁመናው የተስተካከለ መልከ መልካም ሰው ነበር። ከጊዜ በኋላ የጌታው ሚስት ዮሴፍን ተመልክታ ስለ አፈቀረችው፥ “ና ከእኔ ጋር አብረን እንተኛ” አለችው። እርሱ ግን ይህን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፤ ስለዚህም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሁሉንም ነገር በእኔ ኀላፊነት ሥር ስላደረገ፥ በቤቱ ውስጥ ስላለው ንብረት ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፤ ያለውን ንብረት ሁሉ እንዳስተዳድርለት በዐደራ ለእኔ ሰጥቶኛል። ጌታዬ በዚህ ቤት ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት የለውም፤ ከአንቺ በቀር በእኔ ቊጥጥር ሥር ያላደረገው ምንም ነገር የለም፤ ይኸውም ሚስቱ ስለ ሆንሽ ነው፤ ታዲያ ይህን አስከፊ ኃጢአት በመፈጸም እግዚአብሔርን እንዴት አሳዝናለሁ?” እርስዋም ይህንኑ ጉዳይ በየቀኑ ትነግረው ነበር፤ ዮሴፍ ግን አብሮአት መተኛት ወይም በአጠገቧ ለመገኘት አልፈለገም።
ኦሪት ዘፍጥረት 39 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 39:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos