ኦሪት ዘፍጥረት 39
39
ዮሴፍና የጶጢፋር ሚስት
1እስማኤላውያን ነጋዴዎች ዮሴፍን ወደ ግብጽ ወሰዱት፤ እዚያም ከግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ባለሥልጣኖች አንዱ ለሆነው ለጶጢፋር ሸጡት፤ ጶጢፋር የተባለው ግብጻዊ፥ የፈርዖን የዘበኞች አለቃ ነበር። 2እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበር፤ ስለዚህም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ሲኖር ሁሉ ነገር ተቃናለት። #ሐ.ሥ. 7፥9። 3እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር እንደ ነበረና ሥራውንም ሁሉ እንዳቃናለት ባየ ጊዜ፥ 4ጶጢፋር ዮሴፍን ወደደው፤ የቅርብ አገልጋዩም አደረገው፤ በቤቱ ላይ አዛዥነትን፥ በንብረቱም ሁሉ ላይ ኀላፊነትን ሰጠው። 5ይህም ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር በዮሴፍ ምክንያት የግብጻዊውን ሰው ቤት ንብረትና በውጪም በእርሻ ያለውን ሀብት ሁሉ ባረከለት። 6ስለዚህ ጶጢፋር ያለውን ንብረት ሁሉ በዮሴፍ ቊጥጥር ሥር አደረገ፤ ጶጢፋር ከሚመገበው ምግብ በስተቀር የሚያውቀው ምንም ነገር አልነበረም።
ዮሴፍ ቁመናው የተስተካከለ መልከ መልካም ሰው ነበር። 7ከጊዜ በኋላ የጌታው ሚስት ዮሴፍን ተመልክታ ስለ አፈቀረችው፥ “ና ከእኔ ጋር አብረን እንተኛ” አለችው። 8እርሱ ግን ይህን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፤ ስለዚህም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሁሉንም ነገር በእኔ ኀላፊነት ሥር ስላደረገ፥ በቤቱ ውስጥ ስላለው ንብረት ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፤ ያለውን ንብረት ሁሉ እንዳስተዳድርለት በዐደራ ለእኔ ሰጥቶኛል። 9ጌታዬ በዚህ ቤት ባለው ንብረት ሁሉ ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት የለውም፤ ከአንቺ በቀር በእኔ ቊጥጥር ሥር ያላደረገው ምንም ነገር የለም፤ ይኸውም ሚስቱ ስለ ሆንሽ ነው፤ ታዲያ ይህን አስከፊ ኃጢአት በመፈጸም እግዚአብሔርን እንዴት አሳዝናለሁ?” 10እርስዋም ይህንኑ ጉዳይ በየቀኑ ትነግረው ነበር፤ ዮሴፍ ግን አብሮአት መተኛት ወይም በአጠገቧ ለመገኘት አልፈለገም።
11ከዕለታት አንድ ቀን ዮሴፍ ለሥራ ጉዳይ ወደ ቤት ሲገባ በቤት ውስጥ አንድም ሠራተኛ አልነበረም። 12በዚያን ጊዜ የጌታው ሚስት ልብሱን ይዛ “ከእኔ ጋር ተኛ” አለችው፤ እርሱ ግን ልብሱን እጅዋ ላይ ትቶላት ከቤት ሸሽቶ ወጣ። 13እርስዋም ልብሱን በእጅዋ ላይ ትቶ ከቤት ሸሽቶ መውጣቱን በተመለከተች ጊዜ፥ 14አገልጋዮችዋን ጠርታ እንዲህ አለቻቸው፤ “እነሆ፥ ባለቤቴ ያመጣው ይህ ዕብራዊ ሊያዋርደን ነበር፤ ወዳለሁበት ክፍል ገብቶ ሊደፍረኝ ሞከረ፤ እኔ ግን ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽኩ። 15ርዳታ ለማግኘትም መጮኼን በሰማ ጊዜ ልብሱን አጠገቤ ትቶ ከቤት ሸሽቶ ወጣ።”
16የዮሴፍ አሳዳሪ እስኪመጣ ድረስ ልብሱን በእርስዋ ዘንድ አቈየችው። 17በመጣም ጊዜ የሆነውን ታሪክ እንዲህ ስትል ዘርዝራ ነገረችው፥ “አንተ ወደዚህ ያመጣኸው ዕብራዊ አገልጋይ ወዳለሁበት ክፍል ገብቶ ሊያዋርደኝ ነበር። 18ነገር ግን ርዳታ ለማግኘት ድምፄን ከፍ አድርጌ በጮኽኩ ጊዜ ልብሱን አጠገቤ ትቶ ከቤት ሸሽቶ ወጣ።”
19ሚስቱ “የአንተ አገልጋይ እንዲህ አደረገኝ” ብላ የነገረችውን ታሪክ በሰማ ጊዜ የዮሴፍ አሳዳሪ እጅግ ተቈጣ። 20ስለዚህ ዮሴፍን ወስዶ የንጉሡ እስረኞች ወዳሉበት እስር ቤት አስገባው። ነገር ግን ዮሴፍ በእስር ቤት በነበረበት ጊዜ፥ 21እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሆኖ ዘላቂ ፍቅሩን አሳየው፤ በእስር ቤቱ አዛዥ ዘንድ ባለሟልነትን እንዲያገኝ አደረገው። #ሐ.ሥ. 7፥9። 22በዚህ ዐይነት በእስረኞቹ ሁሉ ላይና በእስር ቤቱ ውስጥ በሚደረገው ነገር ሁሉ ላይ ኀላፊ አደረገው። 23እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ሆኖ የሚያደርገው ነገር ሁሉ እንዲቃናለት ስላደረገ የእስር ቤቱ አዛዥ በዮሴፍ ቊጥጥር ሥር በነበረው ነገር ምንም ሐሳብ አልነበረበትም።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 39: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997