በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፣ ግብጻዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው። እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። አሳዳሪውም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወለት ባየ ጊዜ፣ ዮሴፍ በርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ፣ እግዚአብሔር የግብጻዊውን ቤት ባረከ፤ የእግዚአብሔርም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በቀር፣ ማንኛውንም ጕዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር። ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ እያደርም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለች፤ አፍ አውጥታም፣ “ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጕተውም፣ አልሰማትም፤ ከርሷ ጋራ መተኛት ይቅርና ዐብሯትም መሆን አልፈቀደም።
ዘፍጥረት 39 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 39
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 39:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos