ዘፍጥረት 25:27-32
ዘፍጥረት 25:27-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ብላቴኖቹም አደጉ፤ ጐለመሱም፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፤ በቤትም ይቀመጥ ነበር። ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበር፤ እርሱ ከአደነው ይበላ ነበርና። ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች። ለያዕቆብም የምስር ንፍሮ ቀቀለችለት፤ ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤ ዔሳውም ያዕቆብን፥ “ከምስር ንፍሮህ አብላኝ፤ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና” አለው፤ ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕቆብም ዔሳውን፥ “ዛሬ ብኵርናህን ስጠኝ” አለው። ዔሳውም፥ “እነሆ፥ እኔ ልሞት ነኝ፤ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት?” አለ።
ዘፍጥረት 25:27-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጆቹም ዐደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር። ይስሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወድደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድደው ነበር። አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ። ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም፣ “እነሆ፤ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ።
ዘፍጥረት 25:27-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ብላቴኖቹም አደጉ፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በድንኳንም ይቀመጥ ነበር። ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበረ ካደነው ይበላ ነበርና፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች። ያዕቆብም ወጥ ሠራ ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤ ዔሳውም ያዕቆብን፦ ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና አለው ስለዚህ ስሙ ኤዶም ተባለ። ያዕቆብም፦ በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ አለው። ዔሳውም፦ እነሆ እኔ ልሞት ነኝ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት? አለ።
ዘፍጥረት 25:27-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሁለቱም ልጆች አደጉ፤ ዔሳው በዱር መዋል የሚወድ ብልኅ አዳኝ ሆነ፤ ያዕቆብ ግን በቤት መዋል የሚወድ ጭምት ሰው ነበር። ዔሳው እያደነ ሥጋ ያበላው ስለ ነበረ ይስሐቅ ዔሳውን ይወድ ነበር። ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ቀይ የምስር ወጥ በመሥራት ላይ እንዳለ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ ስለዚህም ያዕቆብን “ከዚህ ከቀይ ወጥ ስጠኝ” አለው። ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር። ያዕቆብም “መጀመሪያ ብኲርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም “እኔ በራብ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው።
ዘፍጥረት 25:27-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልጆቹም ባደጉ ጊዜ፥ ዔሳውም በዱር የሚውል ብልኅ አዳኝ ሆነ፥ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፥ በቤትም ይቀመጥ ነበር። ይስሐቅም ዔሳው ካደነው ይበላ ነበርና ይወደው ነበር፥ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ ሲሠራ፥ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ ዔሳውም ያዕቆብን፥ “ከዚህ ከቀዩ ወጥ አብላኝ፥ እኔ እጅግ እርቦኛልና!” አለው፤ (ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር።) ያዕቆብም፥ “በመጀመሪያ ብኩርናህን ሽጥልኝ” አለው። ዔሳውም “እኔ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው።