ኦሪት ዘፍጥረት 25
25
አብርሃም ከኬጡራ የወለዳቸው ልጆች
(1ዜ.መ. 1፥32-33)
1አብርሃምም ደግሞ ስምዋ ኬጡራ የተባለች ሚስት አገባ። 2እርስዋም ዘንበሪን፥ ዮቃጤንን፥ ሜዳንን፥ ዮብቅን፥ ምድያምንና ሴሂን ወለደችለት። 3ዮቃጤንም ሶቤቅን፥ ቲማንንና ድዳንን ወለደ። የድዳንም ልጆች ራጉኤል፥ ንበከዝ፥ እስራኦምና ሎአም ናቸው። 4የምድያምም ልጆች ጌፌር፥ ዔፋር፥ ሄኖኅ፥ አቢሮንና ቲያሮስ ናቸው። እነዚህም ሁሉ የኬጡራ ልጆች ናቸው። 5አብርሃምም በሕይወቱ ሳለ ገንዘቡን ሁሉ ለልጁ ለይስሐቅ ሰጠው፤ 6አብርሃምም ለቁባቶቹ ልጆች ሀብትን ሰጣቸው፤ እርሱም ገና በሕይወቱ ሳለ ከልጁ ከይስሐቅ ለይቶ ወደ ምሥራቅ ሀገር ሰደዳቸው።
የአብርሃም ሞት
7አብርሃምም የኖረበት የዕድሜው ዓመታት እነዚህ ናቸው፤ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ኖረ። 8አብርሃምም መልካም ሽምግልናን ሸምግሎ፥ ዘመኑንም ፈጽሞ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተጨመረ። 9ልጆቹ ይስሐቅና ይስማኤልም በመምሬ ፊት ለፊት ባለው በኬጢያዊው በሰዓር ልጅ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ ቀበሩት። 10ይህም አብርሃም ከኬጢ ልጆች የገዛው እርሻ ነው፤ አብርሃምንና ሚስቱን ሣራን በዚያ ቀበሩአቸው። 11እንዲህም ሆነ፥ አብርሃምም ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር ልጁን ይስሐቅን ባረከው፤ ይስሐቅም ዐዘቅተ ራእይ ተብሎ በሚጠራው ምንጭ አጠገብ ኖረ።
የይስማኤል ትውልድ
(1ዜ.መ. 1፥28-31)
12የሣራ ባሪያ ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት የአብርሃም ልጅ የይስማኤል ትውልድ ይህ ነው፤ 13የይስማኤልም የልጆቹ ስም በየስማቸውና በየትውልዳቸው እንዲህ ነው። 14የይስማኤል የበኵር ልጁ ናቡአት፥ ቄዳር፥ ነብዳኤል፥ መብሳን፥ 15ማሴሜ፥ ዱማ፥ ማሤን፥ ኩዳን፥ ቴማን፥ ኤያጤር፥ ናፌስ፥ ቄድን። 16የይስማኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ስማቸውም በየመንደራቸውና በየሰፈራቸው ይህ ነው፤ በየወገናቸውም ዐሥራ ሁለት አለቆች ናቸው። 17እርሱም ከኤውላጥ አንሥቶ በግብፅ ፊት ለፊት እስከምትገኝ እስከ ሴይር ባለው ሀገር ኖረ፤ ወደ አሦርዮንም ደረሰ፤ እንዲህም ከወንድሞቹ ሁሉ ፊት ተቀመጠ። 18ይስማኤልም የኖረበት የዕድሜው ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው ፤ ሸምግሎ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተጨመረ።#ምዕ. 25 ቁ. 17 እና 18 በዕብ. እና በግሪክ ሰባ ሊ. ተዘዋውረዋል።
የዔሳውና የያዕቆብ መወለድ
19የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ትውልድም ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፥ 20ይስሐቅም ሚስት ትሆነው ዘንድ የሶርያዊውን የላባን እኅት፥ የሶርያዊውን የባቱኤልን ልጅ ርብቃን ከሁለቱ ከሶርያ ወንዞች መካከል በወሰዳት ጊዜ አርባ ዓመት ሆኖት ነበር። 21ይስሐቅም ስለ ሚስቱ ርብቃ ወደ እግዚአብሔር ለመነ፤ መካን ነበረችና፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ሚስቱ ርብቃም ፀነሰች። 22ልጆችዋም በሆድዋ ውስጥ ይንቀሳቀሱ ነበር ፤ እርስዋም፥ “እንዲህ እሆን ዘንድ ካለኝ ይህ ለእኔ ምኔ ነው?” አለች። ወደ እግዚአብሔርም ትለምን ዘንድ ሄደች። 23እግዚአብሔርም አላት፥ “ሁለት ሕዝቦች በማኅፀንሽ አሉ፤ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይወለዳሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል።” 24የምትወልድበትም ወራት ተፈጸመ፤ በማኅፀንዋም መንታ ነበሩ። 25የበኵር ልጅዋም ወጣ፤ እንደ ጽጌረዳም ቀይ ነበረ፤ ሁለንተናውም ጠጕራም ነበር፤ ስሙንም ዔሳው ብላ ጠራችው። 26ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙንም ያዕቆብ ብላ ጠራችው። ርብቃ ዔሳውንና ያዕቆብን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር።
ዔሳው ብኵርናውን እንደ ሰጠ
27ብላቴኖቹም አደጉ፤ ጐለመሱም፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፤ በቤትም ይቀመጥ ነበር። 28ይስሐቅም ዔሳውን ይወድ ነበር፤ እርሱ ከአደነው ይበላ ነበርና። ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበረች። 29ለያዕቆብም የምስር ንፍሮ ቀቀለችለት፤#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ያዕቆብም የምስር ንፍሮ ቀቀለ” ይላል። ዔሳውም ደክሞ ከበረሃ ገባ፤ 30ዔሳውም ያዕቆብን፥ “ከምስር ንፍሮህ አብላኝ፤ እኔ እጅግ ደክሜአለሁና” አለው፤ ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ። 31ያዕቆብም ዔሳውን፥ “ዛሬ ብኵርናህን ስጠኝ” አለው። 32ዔሳውም፥ “እነሆ፥ እኔ ልሞት ነኝ፤ ይህች ብኵርና ለምኔ ናት?” አለ። 33ያዕቆብም፥ “ብኵርናህን ትሰጠኝ ዘንድ እስኪ ዛሬ ማልልኝ” አለው። ዔሳውም ማለለት፤ ብኵርናውንም ለያዕቆብ ሸጠ። 34ያዕቆብም ለዔሳው እንጀራና የምስር ንፍሮ ሰጠው፤ በላ፥ ጠጣ፥ ተነሥቶም ሄደ፤ ዔሳውም ብኵርናውን አቃለላት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 25: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ