ዕዝራ 9:5-15
ዕዝራ 9:5-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሠርክም መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና መጐናጸፊያዬ እንደ ተቀደደ ሆኖ ከመዋረዴ ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጄን ዘረጋሁ። እንዲህም አልሁ፥ “አምላኬ ሆይ፥ ኀጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቶአልና፥ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ብሎአልና አምላኬ ሆይ፥ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፤ እፈራማለሁ። ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ በድለናል፤ ስለ ኀጢአታችን እኛና ልጆቻችን ንጉሦቻችን፥ ካህናቶቻችንም ለሰይፍና ለምርኮ፥ ለብዝበዛና ለዕፍረት በአሕዛብ ነገሥታት እጅ ተጣልን፤ እስከ ዛሬም ድረስ በፊታችን እፍረት እንኖራለን። አሁንም ቅሬታ ይተዉልን ዘንድ፥ በተቀደሰውም ስፍራው ኀይልን ይሰጠን ዘንድ፥ አምላካችንም ዐይናችንን ያበራ ዘንድ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ ለጥቂት ጊዜ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጥቂት ዕረፍትን አገኘን። ባሪያዎቹ ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፤ ቀለባችንን ይሰጡን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት ከፍ ከፍ ያደርጉ ዘንድ፥ የተፈታውንም ይጠግኑ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ያደርጉልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ሞገስን ሰጠን። አሁንስ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? አምላካችን ሆይ፥ ትእዛዝህን ትተናልና። በባሮችህ በነቢያት እጅ ያዘዝሃትን እንዲህ ስትል፦ ትወርሱአት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት የረከሰች ናት፤ በርኵሰታቸውም ከዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ መልተዋታል። አሁንም ትበረቱ ዘንድ፥ የምድሩንም ፍሬ ትበሉ ዘንድ፥ ልጆቻችሁም ለዘለዓለም ይወርሱአት ዘንድ፥ ሴቶችን ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ፤ ሰላማቸውንና ደኅንነታቸውንም ለዘለዓለም አትሹ። ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኀጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም፤ ነገር ግን ድኅነትን ሰጠኸን። ትእዛዝህን እናፈርስ ዘንድ ተመልሰናልና፥ ርኵስ ሥራ ከሚሠሩ ከእነዚህ አሕዛብ ጋርም ተጋብተናልና ከእኛ ከሞት የሚያመልጥ እስከማይኖር ድረስ ፈጽመህ አትቈጣን። አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።”
ዕዝራ 9:5-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም፣ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ የተቀደደውን መጐናጸፊያዬንና ካባዬን እንደ ለበስሁ በሐዘን ከተቀመጥሁበት ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጆቼን በመዘርጋት፣ እንዲህ ስል ጸለይሁ፤ “አምላኬ ሆይ፤ ኀጢአታችን ከራሳችን በላይ ሆኗል፤ በደላችንም እስከ ሰማያት ደርሷል፤ አምላኬ ሆይ፤ ፊቴን ወደ አንተ ቀና ለማድረግ ፈራሁ፤ እጅግም ፈራሁ። ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በደላችን ታላቅ ነው። ከኀጢአታችንም የተነሣ፣ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ እኛም ሆንን፣ ነገሥታቶቻችንና ካህናቶቻችን በባዕዳን ነገሥታት እጅ ወድቀን ለሰይፍ፣ ለምርኮ፣ ለብዝበዛና ለውርደት ተዳርገናል። “አሁን ግን እግዚአብሔር አምላካችን ቅሬታ ይተውልን ዘንድ፣ በመቅደሱም ውስጥ ጽኑ ስፍራ ይሰጠን ዘንድ፣ ለጥቂት ጊዜ ቸርነቱን አሳይቶናል፤ ስለዚህ አምላካችን ለዐይናችን ብርሃን ሰጠን፤ በባርነትም ሳለን ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት ሰጠን። ባሮች ብንሆንም፣ አምላካችን ግን ባሮች ሆነን እንድንቀር አልተወንም፤ ነገር ግን በፋርስ ነገሥታት ፊት ቸርነቱን አሳየን፤ የአምላካችንን ቤት እንደ ገና እንድንሠራና ፍርስራሾቿን እንድንጠግን አዲስ ሕይወት ሰጠን፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የመከላከያ ቅጥር ሰጠን። “አሁን ግን አምላካችን ሆይ፤ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? ትእዛዞችህን አቃልለናልና፤ ያቃለልነውም በባሮችህ በነቢያት አማካይነት፣ ‘ለመውረስ የምትገቡባት ምድር በሕዝቦቿ ርኩሰት ተበክላለች፤ ከዳር እስከ ዳርም በአስጸያፊ ድርጊታቸውና በርኩሰታቸው ተሞልታለች፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ። ብርቱዎች እንድትሆኑ፣ የምድሪቱን መልካም ነገር እንድትበሉና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት እንድታወርሱ ከእነርሱ ጋራ ምንም ዐይነት ውል አታድርጉ’ ብለህ የሰጠኸውን ትእዛዝ ነው። “ይህ ሁሉ የደረሰብን በክፉ ሥራችንና በብዙ በደላችን ምክንያት ነው፤ አምላካችን ሆይ፤ አንተ ግን እንደ በደላችን ብዛት አልቀጣኸንም፤ ይልቁንም ቅሬታን ተውህልን። ታዲያ ትእዛዞችህን እንደ ገና ተላልፈን እንዲህ ያለውን አስጸያፊ ድርጊት ከሚፈጽሙ ሕዝቦች ጋራ መጋባት ተገቢ ነውን? አንተስ ቅሬታ እስከማይኖር ወይም አንድም ሰው እስከማይድን ድረስ ተቈጥተህ አታጠፋንምን? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛም በዚህ ዕለት ተርፈን በሕይወት አለን። እነሆ፣ በፊትህ ከነበደላችን ቀርበናል፤ ከበደላችን የተነሣ ግን በፊትህ ሊቆም የሚችል ማንም የለም።”
ዕዝራ 9:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሠርክም መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና መጐናጸፊያዬ እንደ ተቀደደ ሆኖ ከመዋረዴ ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጄን ዘረጋሁ፤ እንዲህም አልሁ፦ “አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቶአልና፥ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎአልና አምላኬ ሆይ፥ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፤ እፈራማለሁ። ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ በድለናል፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስለ ኃጢአታችን እኛና ንጉሦቻችን፥ ካህናቶቻችንም ለሰይፍና ለምርኮ፥ ለብዝበዛና ለእፍረት በምድር ነገሥታት እጅ ተጣልን። አሁንም ቅሬታ ይተውልን ዘንድ፥ በተቀደሰውም ስፍራው ችንካርን ይሰጠን ዘንድ፥ አምላካችንም ዓይናችንን ያበራ ዘንድ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ ለጥቂት ጊዜ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ሞገስ ተሰጥቶናል። ባሪያዎች ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፤ የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት እንሠራ ዘንድ፥ የተፈታውንም እንጠግን ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ይደረግልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ምሕረቱን ሰጠን። አሁንስ አምላካችን ሆይ፦ ‘ትወርሱአት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት ረክሳለች፤ ከዳር እስከ ዳርም ድረስ ከርኵሰታቸው፥ ከጸያፍ ሥራቸውም ተሞልታለች፤ አሁንም ትበረቱ ዘንድ፥ የምድሩንም ፍሬ ትበሉ ዘንድ፥ ለዘላለምም ለልጆቻችሁ ታወርሱአት ዘንድ ሴቶች ልጆቻችሁን ለልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለልጆቻችሁ አትውሰዱ፤ ሰላማቸውንና ደኅነንታቸውንም ለዘላለም አትሹ’ ብለህ በባሪያዎችህ በነቢያት ያዘዝኸውን ትእዛዝ ትተናልና ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ቅሬታን ሰጠኸን። በውኑ ተመልሰን ትእዛዝህን እናፈርስ ዘንድ፥ ርኩስ ሥራን ከሚሠሩ ከእነዚህም አሕዛብ ጋር እንጋባ ዘንድ ይገባናልን? አንተስ ቅሬታ የሌለንና የማናመልጥ እስክንሆን ድረስ እንድታጠፋን አትቈጣንም? አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።”
ዕዝራ 9:5-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የምሽትም መሥዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ በሐዘን ከተቀመጥኩበት ስፍራ ተነሣሁ፤ የቀደድኩትን ልብስ እንደ ለበስኩ፥ በጒልበቴም በመንበርከክ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጆቼን ዘርግቼ እንዲህ ስል ጸለይኩ፦ “አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን ከራሳችን በላይ ስለ ሆነና በደላችንም ወደ ሰማይ ስለ ደረሰ ፊቴን ወደ አምላኬ ወደ አንተ ለማቅናት ዐፍራለሁ እፈራለሁም። ከቀድሞ አባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እኛ ታላቅ በደል ሠርተናል፤ ከኃጢአታችንም ብዛት የተነሣ እኛ፥ ነገሥታቶችንና ካህናታችን በባዕዳን ነገሥታት እጅ ወድቀናል፤ ስለዚህም ለሰይፍ ተዳረግን፤ ሀብታችንንም ተዘረፍን፤ በመታሰር ተማርከን ተወሰድን፤ እነሆ፥ አሁንም እንዳለንበት ሁኔታ እስከ መጨረሻ ተዋርደናል። አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ዐይናችንን አበራህ፤ እነሆ፥ አሁን ደግሞ ለጥቂት ጊዜ በፊትህ ሞገስን አግኝተን ከእኛ ጥቂቶቹ ከባርነት ቀንበር ነጻ ወጥተው በዚህች ቅድስት ምድር በሰላም ይኖሩ ዘንድ ፈቅደሃል፤ ምንም እንኳ በባርነት አገዛዝ ሥር ብንወድቅም እነሆ አዲስ ሕይወት ሰጥተኸናል። እኛ ባርያዎች ነበርን፤ አንተ ግን ባርያዎች ሆነን እንድንቀር አልተውከንም፤ አንተ የፋርስ ነገሥታት እንዲራሩልንና በሕይወት ነጻ ወጥተን ቀደም ሲል ፈርሶ የነበረውን ቤተ መቅደስህን እንደገና መልሰን እንድንሠራ፥ እዚህም በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሰላም እንድንኖር ፈቀድክልን። “ነገር ግን አምላካችን ሆይ! እስከ አሁን ስለ ሆነው ነገር ሁሉ ምን ማለት እንችላለን? እነሆ፥ አሁንም እንደገና ትእዛዞችህ አላከበርንም፤ እነዚህም ትእዛዞች በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካይነት የተሰጡ ነበሩ፤ ነቢያት አስቀድመው ‘የምትወርሱአት ምድር ከርኲሰት ሁሉ የነጻች አይደለችም፤ የሚኖሩባት ሕዝቦች ዳር እስከ ዳር በአጸያፊ ተግባር ሁሉ እንድትሞላ አድርገዋታል። ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን በጋብቻ ለእነርሱ ወንዶች ልጆች አትስጡ፤ እናንተም ለወንዶች ልጆቻችሁ የእነርሱን ሴቶች ልጆች በጋብቻ አትውሰዱ፤ በማንኛውም ጊዜ ከምድሩ መልካም ነገር በልታችሁ ለልጆቻችሁ ዘላቂ ርስት አድርጋችሁ ለማስተላለፍ እንድትችሉ በማንኛውም ጊዜ ከእነርሱ ጋር የወዳጅነት ስምምነት አታድርጉ’ ሲሉ ነግረውን ነበር። የደረሰብን ችግር የክፉ ሥራችንና የበደላችን ውጤት ነው፤ ሆኖም አምላካችን የቀጣኸን ልንቀጣ ከሚገባን ያነሰ ነው፤ ከዚህም በላይ ከሞት አምልጠን በሕይወት አትርፈኸናል። ታዲያ እንዴት እንደገና የአንተን ትእዛዞች ጥሰን ከእነዚህ ዐመፀኞች ሕዝቦች ጋር ጋብቻ እንፈጽማለን? በዚህስ ምክንያት ምንም ቅሬታ ሳታስቀርልን እኛን በቊጣህ አታጠፋንምን? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ ፈራጅ ነህ፤ ነገር ግን ከጥፋት አምልጠን በሕይወት እንድንኖር ፈቀድክልን፤ እነሆ እኛ፥ በደላችንን ተሸክመን በፊትህ ለመቅረብ የተገባን አይደለንም።”
ዕዝራ 9:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በሠርክ መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና ካባዬ እንደተቀደደ ከተዋረድኩበት ተነሣሁ፥ በጉልበቴም ተንበርክኬ ወደ ጌታ አምላኬ እጄን ዘረጋሁ፤ እንዲህም አልሁ፦ “አምላኬ ሆይ፥ አፍሬአለሁ፤ አምላኬ ሆይ፥ ፊቴንም ወደ አንተ ለማንሣት እፈራለሁ፥ ኃጢአታችን ከራሳችን በላይ ከፍ ብሏልና፥ በደላችንም ወደ ሰማያት ወጥቷልና። ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ በታላቅ በደል ነበርን፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስለ ኃጢአታችን እኛ፥ ነገሥታቶችንና ካህናቶቻችን ለሰይፍ፥ ለምርኮ፥ ለብዝበዛና ለእፍረት በምድር ነገሥታት እጅ ተሰጠን። አሁንም ትሩፋን እንዲያስቀርልን፥ በተቀደሰውም ስፍራው ችንካርን እንዲሰጠን፥ አምላካችንም ዓይናችንን እንዲያበራ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን እንዲሰጠን ለጥቂት ጊዜ ከጌታ ከአምላካችን ሞገስ ተሰጥቶናል። ባርያዎች ነን፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፥ የአምላካችንን ቤት እንድንሠራና ፍርስራሾቹን እንድንጠግን መታደስን ሊሰጠን፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ግንብ ሊሰጠን በፋርስ ነገሥታት ፊት ፅኑ ፍቅሩን በእኛ ላይ ዘረጋ። ስለዚህ አምላካችን ሆይ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? ትእዛዛትህን ትተናልና፤ በአገልጋዮችህ በነቢያት እንዲህ ስትል ያዘዝኸውን ‘ልትወርሱአት የምትገቡባት ምድር፥ በምድሩ ሕዝቦች ርኩሰት የረከሰች ምድር ናት፤ ከዳር እስከ ዳርም በርኩሰታቸውና በአጸያፊ ተግባራቸው ተሞልታለች። ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ፥ ሰላማቸውንና ደኅነንታቸውንም ለዘለዓለም አትሹ። ይህም እንድትበረቱ፥ የምድሩንም መልካም ነገር እንድትበሉ፥ ለልጆቻችሁ ለዘለዓለምም ውርስ እንድታወርሱ ነው።’” በክፉ ሥራችንና በታላቁ በደላችን ከደረሰብን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ትሩፋንን ሰጠኸን። ትእዛዝህን ለማፍረስ፥ ርኩስ ሥራን ከሚሠሩ ከእነዚህም ሕዝቦች ጋር ለመጋባት እንመለሳለንን? አንተስ ትሩፋን የሌለንና የማናመልጥ እስክንሆን ድረስ እንድታጠፋን አትቆጣምን? የእስራኤል አምላክ ጌታ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥ እንደ ዛሬው እኛ አምልጠን ቀርተናል፥ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፥ በዚህ ምክንያት በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።