በሠርክም መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና መጐናጸፊያዬ እንደ ተቀደደ ሆኖ ከመዋረዴ ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጄን ዘረጋሁ። እንዲህም አልሁ፥ “አምላኬ ሆይ፥ ኀጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቶአልና፥ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ብሎአልና አምላኬ ሆይ፥ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፤ እፈራማለሁ። ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ በድለናል፤ ስለ ኀጢአታችን እኛና ልጆቻችን ንጉሦቻችን፥ ካህናቶቻችንም ለሰይፍና ለምርኮ፥ ለብዝበዛና ለዕፍረት በአሕዛብ ነገሥታት እጅ ተጣልን፤ እስከ ዛሬም ድረስ በፊታችን እፍረት እንኖራለን። አሁንም ቅሬታ ይተዉልን ዘንድ፥ በተቀደሰውም ስፍራው ኀይልን ይሰጠን ዘንድ፥ አምላካችንም ዐይናችንን ያበራ ዘንድ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ ለጥቂት ጊዜ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጥቂት ዕረፍትን አገኘን። ባሪያዎቹ ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፤ ቀለባችንን ይሰጡን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት ከፍ ከፍ ያደርጉ ዘንድ፥ የተፈታውንም ይጠግኑ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ያደርጉልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ሞገስን ሰጠን። አሁንስ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? አምላካችን ሆይ፥ ትእዛዝህን ትተናልና። በባሮችህ በነቢያት እጅ ያዘዝሃትን እንዲህ ስትል፦ ትወርሱአት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት የረከሰች ናት፤ በርኵሰታቸውም ከዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ መልተዋታል። አሁንም ትበረቱ ዘንድ፥ የምድሩንም ፍሬ ትበሉ ዘንድ፥ ልጆቻችሁም ለዘለዓለም ይወርሱአት ዘንድ፥ ሴቶችን ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ፤ ሰላማቸውንና ደኅንነታቸውንም ለዘለዓለም አትሹ። ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኀጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም፤ ነገር ግን ድኅነትን ሰጠኸን። ትእዛዝህን እናፈርስ ዘንድ ተመልሰናልና፥ ርኵስ ሥራ ከሚሠሩ ከእነዚህ አሕዛብ ጋርም ተጋብተናልና ከእኛ ከሞት የሚያመልጥ እስከማይኖር ድረስ ፈጽመህ አትቈጣን። አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።”
መጽሐፈ ዕዝራ 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዕዝራ 9:5-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች