ከዚያም፣ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ የተቀደደውን መጐናጸፊያዬንና ካባዬን እንደ ለበስሁ በሐዘን ከተቀመጥሁበት ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጆቼን በመዘርጋት፣ እንዲህ ስል ጸለይሁ፤ “አምላኬ ሆይ፤ ኀጢአታችን ከራሳችን በላይ ሆኗል፤ በደላችንም እስከ ሰማያት ደርሷል፤ አምላኬ ሆይ፤ ፊቴን ወደ አንተ ቀና ለማድረግ ፈራሁ፤ እጅግም ፈራሁ። ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በደላችን ታላቅ ነው። ከኀጢአታችንም የተነሣ፣ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ እኛም ሆንን፣ ነገሥታቶቻችንና ካህናቶቻችን በባዕዳን ነገሥታት እጅ ወድቀን ለሰይፍ፣ ለምርኮ፣ ለብዝበዛና ለውርደት ተዳርገናል። “አሁን ግን እግዚአብሔር አምላካችን ቅሬታ ይተውልን ዘንድ፣ በመቅደሱም ውስጥ ጽኑ ስፍራ ይሰጠን ዘንድ፣ ለጥቂት ጊዜ ቸርነቱን አሳይቶናል፤ ስለዚህ አምላካችን ለዐይናችን ብርሃን ሰጠን፤ በባርነትም ሳለን ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት ሰጠን። ባሮች ብንሆንም፣ አምላካችን ግን ባሮች ሆነን እንድንቀር አልተወንም፤ ነገር ግን በፋርስ ነገሥታት ፊት ቸርነቱን አሳየን፤ የአምላካችንን ቤት እንደ ገና እንድንሠራና ፍርስራሾቿን እንድንጠግን አዲስ ሕይወት ሰጠን፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የመከላከያ ቅጥር ሰጠን። “አሁን ግን አምላካችን ሆይ፤ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? ትእዛዞችህን አቃልለናልና፤ ያቃለልነውም በባሮችህ በነቢያት አማካይነት፣ ‘ለመውረስ የምትገቡባት ምድር በሕዝቦቿ ርኩሰት ተበክላለች፤ ከዳር እስከ ዳርም በአስጸያፊ ድርጊታቸውና በርኩሰታቸው ተሞልታለች፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ። ብርቱዎች እንድትሆኑ፣ የምድሪቱን መልካም ነገር እንድትበሉና ለልጆቻችሁም የዘላለም ርስት እንድታወርሱ ከእነርሱ ጋራ ምንም ዐይነት ውል አታድርጉ’ ብለህ የሰጠኸውን ትእዛዝ ነው። “ይህ ሁሉ የደረሰብን በክፉ ሥራችንና በብዙ በደላችን ምክንያት ነው፤ አምላካችን ሆይ፤ አንተ ግን እንደ በደላችን ብዛት አልቀጣኸንም፤ ይልቁንም ቅሬታን ተውህልን። ታዲያ ትእዛዞችህን እንደ ገና ተላልፈን እንዲህ ያለውን አስጸያፊ ድርጊት ከሚፈጽሙ ሕዝቦች ጋራ መጋባት ተገቢ ነውን? አንተስ ቅሬታ እስከማይኖር ወይም አንድም ሰው እስከማይድን ድረስ ተቈጥተህ አታጠፋንምን? የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ እኛም በዚህ ዕለት ተርፈን በሕይወት አለን። እነሆ፣ በፊትህ ከነበደላችን ቀርበናል፤ ከበደላችን የተነሣ ግን በፊትህ ሊቆም የሚችል ማንም የለም።”
ዕዝራ 9 ያንብቡ
ያዳምጡ ዕዝራ 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዕዝራ 9:5-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች