መጽሐፈ ዕዝራ 9

9
ከባዕዳን ጋር ስለተፈጸመው ጋብቻ የዕዝራ የንስሓ ጸሎት
1ይህም ከተፈጸመ በኋላ አለቆቹ ወደ እኔ ቀርበው፦ “የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ እንደ ከነዓናውያን፥ እንደ ኬጢያውያን፥ እንደ ፌርዛውያን፥ እንደ ኢያቡሳውያን፥ እንደ አሞናውያን፥ እንደ ሞዓባውያን፥ እንደ ግብጻውያንና እንደ አሞራውያን ርኵሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር አሕዛብ አልተለዩም፤ 2ለራሳቸውና ለልጆቻቸውም ሴቶች ልጆቻቸውን ወስደዋል፤ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር አሕዛብ ጋር ደባልቀዋል፤ አስቀድሞም አለቆቹና ሹማምንቶቹ በዚህ መተላለፍ መጀመሪያ ሆነዋል” አሉኝ። 3ይህንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና መጐናጸፊያዬን ቀደድሁ፤ የራሴንና የጢሜንም ጠጉር ነጨሁ፤ ደንግጬም ተቀመጥሁ። 4ስለ ምርኮኞቹም መተላለፍ የእስራኤልን አምላክ ቃል የሚፈሩ ሁሉ ወደ እኔ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ ደንግጬ ተቀመጥሁ።
5በሠርክም መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና መጐናጸፊያዬ እንደ ተቀደደ ሆኖ ከመዋረዴ ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጄን ዘረጋሁ፤ 6እንዲህም አልሁ፦ “አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቶአልና፥ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎአልና አምላኬ ሆይ፥ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፤ እፈራማለሁ። 7ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ በድለናል፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስለ ኃጢአታችን እኛና ንጉሦቻችን፥ ካህናቶቻችንም ለሰይፍና ለምርኮ፥ ለብዝበዛና ለእፍረት በምድር ነገሥታት እጅ ተጣልን። 8አሁንም ቅሬታ ይተውልን ዘንድ፥ በተቀደሰውም ስፍራው ችንካርን ይሰጠን ዘንድ፥ አምላካችንም ዓይናችንን ያበራ ዘንድ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ ለጥቂት ጊዜ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ሞገስ ተሰጥቶናል። 9ባሪያዎች ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፤ የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት እንሠራ ዘንድ፥ የተፈታውንም እንጠግን ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ይደረግልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ምሕረቱን ሰጠን። 10-12አሁንስ አምላካችን ሆይ፦ ‘ትወርሱአት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት ረክሳለች፤ ከዳር እስከ ዳርም ድረስ ከርኵሰታቸው፥ ከጸያፍ ሥራቸውም ተሞልታለች፤ አሁንም ትበረቱ ዘንድ፥ የምድሩንም ፍሬ ትበሉ ዘንድ፥ ለዘላለምም ለልጆቻችሁ ታወርሱአት ዘንድ ሴቶች ልጆቻችሁን ለልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለልጆቻችሁ አትውሰዱ፤ ሰላማቸውንና ደኅነንታቸውንም ለዘላለም አትሹ’ ብለህ በባሪያዎችህ በነቢያት ያዘዝኸውን ትእዛዝ ትተናልና ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? 13ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ቅሬታን ሰጠኸን። 14በውኑ ተመልሰን ትእዛዝህን እናፈርስ ዘንድ፥ ርኩስ ሥራን ከሚሠሩ ከእነዚህም አሕዛብ ጋር እንጋባ ዘንድ ይገባናልን? አንተስ ቅሬታ የሌለንና የማናመልጥ እስክንሆን ድረስ እንድታጠፋን አትቈጣንም? 15አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ