ዕዝራ 6:13-22
ዕዝራ 6:13-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ ደግሞ አስተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድ ሽማግሌዎችና ሌዋውያንም በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት መሠረት ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤልም አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስና እንደ ዳርዮስ፥ እንደ አርተሰስታም ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። የእስራኤልም ልጆች ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ የቀሩትም የምርኮኞች ልጆች የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ። በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች፥ አራት መቶም የበግ ጠቦቶች አቀረቡ፤ ስለ ኀጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው፥ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው አቆሙ። የምርኮኞቹም ልጆች በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ። ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሓን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ልጆች ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸው ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም የፋሲካውን በግ ዐረዱ። ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ ፋሲካውን በሉ፤ እግዚአብሔርም ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።
ዕዝራ 6:13-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ንጉሡ ዳርዮስ ባዘዘው መሠረት በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሥራው በትጋት እንዲፈጸም አደረጉ። ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተጽናኑ ሥራውን ቀጠሉ፤ የቤተ መቅደሱንም ሥራ በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ እንዲሁም የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፣ ዳርዮስና አርጤክስስ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ሠርተው ጨረሱ። ይህም ቤተ መቅደስ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በሦስተኛው ቀን ተጠናቀቀ። ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና የቀሩትም ምርኮኞች የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ። ለዚህ ለእግዚአብሔር ቤት ምረቃም አንድ መቶ ወይፈኖችን፣ ሁለት መቶ አውራ በጎችንና አራት መቶ ተባዕት ጠቦቶችን ሰጡ፤ ለመላው እስራኤል የኀጢአት መሥዋዕትም ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ልክ አቀረቡ። በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላክ አገልግሎት ካህናቱን በየማዕረጋቸው፣ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቧቸው። ምርኮኞቹ በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ። ካህናቱና ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ሁሉም በሥርዐቱ መሠረት ነጽተው ነበር። ሌዋውያኑም የፋሲካውን በግ ለምርኮኞቹ ሁሉ፣ ለካህናት ወንድሞቻቸውና ለራሳቸው ዐረዱ። ስለዚህ ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በአምልኮ ይፈልጉት ዘንድ ራሳቸውን ከአረማውያን ጎረቤቶቻቸው ርኩሰት ከለዩት ሁሉ ጋራ በሉ። እግዚአብሔር ደስ እንዲሰኙ ስላደረጋቸው የቂጣን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አከበሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የአሦርን ንጉሥ ልብ ለውጦ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ቤት ሥራ እንዲያግዛቸው አድርጎ ነበር።
ዕዝራ 6:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ እና ተባባሪዎቻቸው እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤል አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስ፥ እንደ ዳርዮስና እንደ አርጤክስስ ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። የእስራኤልም ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን፥ የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ። በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች፥ አራት መቶም ጠቦቶች አቀረቡ፤ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው፥ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው አቆሙ። ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ። ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም የፋሲካውን በግ አረዱ። ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉ፤ እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።
ዕዝራ 6:13-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ አገረ ገዢው ታተናይ፥ ሸታርቦዝናይና የእነርሱም ተባባሪዎች የሆኑ ባለሥልጣኖች ንጉሠ ነገሥቱ እንዳዘዛቸው ሁሉንም ነገር ፈጸሙ። የአይሁድ መሪዎች፥ ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ እያበረታቱአቸው የቤተ መቅደሱን ሥራ አፋጠኑት፤ በእስራኤል አምላክ ፈቃድ የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፥ ዳርዮስና አርጤክስስ ባዘዙትም መሠረት የቤተ መቅደሱን ሥራ ፈጸሙ፤ የቤተ መቅደሱን ሥራ የፈጸሙትም ዳርዮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ የሚጠራው ወር በገባ በሦስተኛው ቀን ነበር። ከዚህም ቀጥሎ የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ እንዲሁም ከምርኮ የተመለሱት ሌሎችም ሰዎች ሁሉ፥ የቤተ መቅደሱን ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ። እነርሱም ሁሉ ለበዓሉ የሚሆኑትን አንድ መቶ ወይፈኖችን፥ ሁለት መቶ በጎችንና አራት መቶ ጠቦቶችን ለመሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚሆኑም ዐሥራ ሁለት ፍየሎችን በእያንዳንዱ ነገድ ስም አቀረቡ። በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈውም መመሪያ መሠረት በኢየሩሳሌም ለተሠራው ቤተ መቅደስ አገልግሎት፥ ካህናቱን በየክፍላቸው፥ ሌዋውያኑን በየቡድናቸው አደራጁ። ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ። ካህናቱና ሌዋውያኑም ሁሉ በሥርዓቱ መሠረት ራሳቸውን አነጹ፤ ሌዋውያኑም በፋሲካው በዓል አከባበር ላይ ከምርኮ ለተመለሱት ሕዝብና ለካህናቱ፥ እንዲሁም ለራሳቸው የቀረቡትን እንስሶች ዐረዱ። መሥዋዕቱንም ሁሉ ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን እንዲሁም በዚያች ምድር የሚኖሩትን የአሕዛብን ሥርዓት ትተው የነበረውን ልማድ ትተው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሁሉ እንዲመገቡት ተደረገ። እግዚአብሔር ራሱ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ዘንድ መወደድን አግኝተው የእስራኤል አምላክ የሚመሰገንበትን ቤተ መቅደስ እንደገና መሥራት ይችሉ ዘንድ በሥራቸው ሁሉ እንዲረዳቸው ስላደረገላቸው የቂጣን በዓል ሰባት ቀን ሙሉ በታላቅ ደስታ አከበሩ።
ዕዝራ 6:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚያ በኋላ በወንዝ ማዶ ያለ አካባቢ ገዢ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይና ተባባሪዎቻቸው ንጉሡ ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ ሐጌና በዒዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተበረታቱ ሠሩ ተከናወነላቸውም። በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ቂሮስ ትእዛዝ እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስ የፋርስ ንጉሥ ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። የእስራኤል ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በደስታ አከበሩ። ለዚህ የእግዚአብሔር ቤት ምረቃ አንድ መቶ ወይፈኖች፥ ሁለት መቶ አውራ በጎች፥ አራት መቶ የበግ ጠቦቶችን፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። በሙሴም መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕረጋቸው ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቡአቸው። ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አከበሩ። ካህናቱና ሌዋውያኑ እንደ አንድ ሰው ሆነው እራሳቸውን አነጹ፥ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፥ ከምርኮ ለተመለሱ ሕዝቦች ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸው ለካህናቱና ለራሳቸው ፋሲካውን አረዱ። ከምርኮ የተመለሱት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኩሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉት። ጌታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤትም ለመሥራት እጃቸውን እንዲያጸኑ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አከበሩ።