ዕዝራ 6:1-15
ዕዝራ 6:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያ ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ በባቢሎን ቤተ መዛግብት ያሉ የታሪክ መጻሕፍት እንዲመረመሩ አዘዘ። በሜዶን አውራጃ ባለው ባሪ በሚባል ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅልል ተገኘ፤ በውስጡም ይህ ነገር ለመታሰቢያ ተጽፎ ነበር። በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ በኢየሩሳሌም ስላለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ አዘዘ፥ “ይህ ቤት ይሠራ መሥዋዕት የሚቀርብበትም ቦታ ይሠራ፤ ቁመቱም ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን። በሦስት ተራ ታላላቅ ድንጋይ፥ በአንድ ተራ እንጨት ይደረግ፤ ወጭውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ። ናቡከደነዖርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃ ይሰጥ፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ይኑር። “አሁንም አንተ በወንዝ ማዶ ያለኸው የሀገሩ ገዥ ተንትናይ ደግሞ አሰተርቡዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻችሁ አፈርስካውያን ከዚያ ራቁ፤ ይህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ ተዉ፤ የአይሁድም አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው ይሥሩ። ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን፥ በወንዝ ማዶ ካለው ሀገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጭውን በትጋት እንድትሰጡአቸው፥ ሥራም እንዳታስፈቱአቸው አዝዣለሁ። ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን ወይፈኖችና አውራ በጎች፥ ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌምም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው፥ የወይን ጠጅና ዘይት የሚጠይቋችሁን ዕለት ዕለት ስጡአቸው። ይኸውም ለሰማይ አምላክ በጎ መዓዛ የሆነውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ለንጉሡና ለልጆቹም ዕድሜ ይጸልዩ ዘንድ ነው። ይህንም ትእዛዝ የሚለውጥ ሁሉ ምሰሶው ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰቀልበት፤ በላዩም ይገደል፤ ቤቱም የጕድፍ መጣያ ይደረግ ብዬ አዝዣለሁ። ስሙ በዚያ የሚኖር አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ፥ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፤ በትጋት ይፈጸም።” ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ ደግሞ አስተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድ ሽማግሌዎችና ሌዋውያንም በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት መሠረት ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤልም አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስና እንደ ዳርዮስ፥ እንደ አርተሰስታም ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ።
ዕዝራ 6:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ንጉሥ ዳርዮስ በባቢሎን ግምጃ ቤት የተቀመጡት መዛግብት እንዲመረመሩ ትእዛዝ ሰጠ። በሜዶን አውራጃ በሚገኘው በአሕምታ ከተማ አንድ ጥቅልል ብራና ተገኘ፤ በውስጡም እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎበት ነበር፤ ማስታወሻ፤ በንጉሥ ቂሮስ የመጀመሪያው ዓመት በኢየሩሳሌም ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ንጉሡ የሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፤ ቤተ መቅደሱ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ ሆኖ እንደ ገና ይሠራ፤ መሠረቱም ይጣል፤ ቁመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን፤ በሦስት ዙር ታላላቅ ድንጋዮችና በአንድ ዙር ዕንጨት ይሠራ፤ ወጪውም ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ይከፈል። እንዲሁም ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች፣ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቦታቸው ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲመለሱ ይሁን፤ በእግዚአብሔርም ቤት ይቀመጡ። አሁንም በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የሆንኸው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና እናንተም በዚያ አውራጃ የምትገኙ ተባባሪዎቻቸው ሁሉ ወደዚያ አትድረሱ። በዚህም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ጣልቃ አትግቡ፤ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት የአይሁድ አገረ ገዥና የአይሁድ መሪዎች በቀድሞው ቦታ ላይ መልሰው ይሥሩት። በተጨማሪም የአይሁድ መሪዎች ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና ሲሠሩ፣ እናንተ ምን እንደምታደርጉላቸው ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ ሥራውም እንዳይቋረጥ የእነዚህ ሰዎች ወጪ በሙሉ ከመንግሥት ግምጃ ቤትና ከኤፍራጥስ ማዶ ከሚገኘው ገቢ ላይ ይከፈል። ለሰማይ አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆን ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ነገር፣ ማለት ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ተባዕት ጠቦቶችን ስጧቸው፤ እንዲሁም ስንዴው፣ ጨዉ፣ የወይን ጠጁና ዘይቱ በኢየሩሳሌም ያሉት ካህናት በሚጠይቋችሁ መሠረት ያለ ማቋረጥ በየቀኑ ይሰጣቸው። ይህ የሚሆነው የሰማይ አምላክን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ ለንጉሡና ለወንድ ልጆቹም ደኅንነት እንዲጸልዩ ነው። ደግሞም ይህን ትእዛዝ የሚለውጥ ማንም ሰው ቢኖር፣ ከቤቱ ምሰሶ ተነቅሎ በምሰሶው ላይ እንዲሰቀል፣ ስለ ወንጀሉም ቤቱ የቈሻሻ መጣያ እንዲሆን አዝዣለሁ። ይህን ትእዛዝ ለማፍረስ ወይም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለማጥፋት እጁን የሚያነሣ ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ፣ ስሙን በዚያ እንዲኖር ያደረገ አምላክ ያጥፋው። እኔ ዳርዮስ በትጋት እንዲፈጸም ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። ከዚያም ንጉሡ ዳርዮስ ባዘዘው መሠረት በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሥራው በትጋት እንዲፈጸም አደረጉ። ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተጽናኑ ሥራውን ቀጠሉ፤ የቤተ መቅደሱንም ሥራ በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ እንዲሁም የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፣ ዳርዮስና አርጤክስስ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ሠርተው ጨረሱ። ይህም ቤተ መቅደስ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በሦስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።
ዕዝራ 6:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያ ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ መዛግብት ባሉበት በባቢሎን ቤተ መጻሕፍት እንዲመረመር አዘዘ። በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅልል ተገኘ፤ በውስጡም ይህ ነገር ለመታሰቢያ ተጽፎ ነበር። በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ እንዲህ ብሎ አዘዘ፤ በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት፥ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፤ በጽኑም ይመሥረት፤ ቁመቱ ስድሳ፥ ክንድ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን። በሦስት ተራ ታላላቅ ድንጋይ፥ በአንድ ተራ እንጨት ይደረግ፤ ወጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ። ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃ ይመለስ፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፤ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር። “አሁንም አንተ በወንዝ ማዶ ያለኸው የአገር ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ እና በወንዝ ማዶ ያሉ ተባባሪዎቻችሁ አፈርስካውያን ከዚያ ራቁ፤ ይህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ ተዉ፤ የአይሁድ አለቃና የአይሁድ ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው ይሠሩ ዘንድ ተዉአቸው። ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት እንድትሰጡአቸው፥ ሥራም እንዳታስፈቱአቸው አዝዣለሁ። ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖች፥ አውራ በጎችና ጠቦቶች፥ በኢየሩሳሌም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው። ይኸውም ለሰማይ አምላክ ጣፋጭ ሽቱ የሆነውን መሥዋዕት ያቀረቡ ዘንድ ለንጉሥና ለልጆቹም ዕድሜ ይጸልዩ ዘንድ ነው። ይህንም ትእዛዝ የሚለውጥ ሁሉ፥ ምሰሶው ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰቀልበት፤ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይደረግ ብዬ አዝዣለሁ። ስሙንም በዚያ ያኖረው አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ በትጋት ይፈጸም።” ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ እና ተባባሪዎቻቸው እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤል አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስ፥ እንደ ዳርዮስና እንደ አርጤክስስ ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ።
ዕዝራ 6:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በባቢሎን ቤተ መንግሥት የሚገኙ መዛግብት ሁሉ ይመረመሩ ዘንድ ንጉሠ ነገሥት ዳርዮስ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ነገር ግን በባቢሎን ከተማ ሳይሆን በሜዶን ክፍለ ሀገር በተለይ “አሕምታ” ተብላ በምትጠራው ከተማ ውስጥ አንድ የብራና ጥቅል ተገኘ፤ በውስጡም የተጻፈበት ቃል እንዲህ የሚል ነበር፦ “ቂሮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ የሚቃጠለውና ሌላውም ልዩ ልዩ መሥዋዕት ይቀርብበት ዘንድ እንደገና እንዲሠራ በመፍቀድ ትእዛዝ ሰጥቶአል፤ የቤተ መቅደሱም ርዝመት ኻያ ሰባት ሜትር፥ ስፋቱም ኻያ ሰባት ሜትር መሆን አለበት። ቅጽሮቹም ከድንጋይ በተሠሩት በሦስቱም ዙር ግንቦች አናት ላይ አንዳንድ ዙር ከእንጨት የተሠራ ድምድማት ይኑራቸው፤ ለዚህም ሁሉ ሥራ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ወጪ ሆኖ ይሰጥ። እንዲሁም ከዚህ በፊት ንጉሥ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ማርኮ ያወጣቸው ከወርቅና ከብር የተሠሩትም ንዋያተ ቅድሳት ወደዚያው ተመልሰው በኢየሩሳሌም በሚሠራው ቤተ መቅደስ በተገቢ ቦታቸው ይቀመጡ።” ከዚህ በኋላ ዳርዮስ የሚከተለውን መልእክት አስተላለፈ፦ “የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ ለሆንከው ለታተናይ፥ ለሸታርቦዝናይና በኤፍራጥስ ምዕራብ ለሚገኙ ተባባሪዎቻችሁ ሁሉ፦ ከቤተ መቅደሱ ራቁ፤ ሥራውን ከማደናቀፍ ተቈጠቡ፤ የይሁዳ ክፍለ ሀገር ገዢና የአይሁድ መሪዎች ቀድሞ በነበረበት ስፍራ ላይ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መልሰው ይሥሩ። በዚሁ አጋጣሚ ይልቁንም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንድታግዙአቸው አዝዣችኋለሁ። ስለዚህም አስፈላጊው የማሠሪያ ገንዘብ ሁሉ ከኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ከተሰበሰበው የመንግሥት ግብር ሳይዘገይ ወጪ እየሆነ ይሰጣቸው፤ ሥራውም መሰናከል አይገባውም። ከዚህም ሁሉ ጋር በኢየሩሳሌም የሚገኙት ካህናት በሚነግሩአችሁ መሠረት በየዕለቱ በሰማይ ለሚኖረው አምላክ ለሚያቀርቡት መሥዋዕት የሚፈልጓቸውን ኰርማዎች፥ በጎችን ወይም ጠቦቶችን፥ እንዲሁም ለመባ የሚሆነውን ስንዴ፥ ጨው፥ የወይን ጠጅና የወይራ ዘይት ሁሉ ስጡአቸው። ይህም ሁሉ የሚሆንበት ምክንያት የሰማይ አምላክ በደስታ የሚቀበለውን መሥዋዕት ሁሉ በማቅረብ ለእኔና ለልጆቼ ሕይወት እንዲጸልዩልን ነው፤ ከዚህም ሌላ ማስታወቅ የምፈልገው ነገር ይህን መመሪያ የማይቀበልና የማይታዘዝ ማንም ሰው ቢኖር ከቤቱ የእንጨት ምሰሶዎች አንዱ ተነቅሎ በአንዱ ጫፍ በኩል እንዲሾል ከተደረገ በኋላ በሰውነቱ ላይ ይሰካበት፤ ቤቱም ፈራርሶ የጉድፍ መጣያ ይሁን። ይህን ትእዛዝ ባለመቀበል በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማፍረስ የሚሞክረውን ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ የስሙ መጠሪያ ይሆን ዘንድ የመረጠ አምላክ ያስወግደው፤ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፍኩ እኔ ዳርዮስ ስለ ሆንኩ በሙሉ መፈጸም አለበት።” ከዚህ በኋላ አገረ ገዢው ታተናይ፥ ሸታርቦዝናይና የእነርሱም ተባባሪዎች የሆኑ ባለሥልጣኖች ንጉሠ ነገሥቱ እንዳዘዛቸው ሁሉንም ነገር ፈጸሙ። የአይሁድ መሪዎች፥ ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ እያበረታቱአቸው የቤተ መቅደሱን ሥራ አፋጠኑት፤ በእስራኤል አምላክ ፈቃድ የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፥ ዳርዮስና አርጤክስስ ባዘዙትም መሠረት የቤተ መቅደሱን ሥራ ፈጸሙ፤ የቤተ መቅደሱን ሥራ የፈጸሙትም ዳርዮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ የሚጠራው ወር በገባ በሦስተኛው ቀን ነበር።
ዕዝራ 6:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚን ጊዜ ንጉሡ ዳርዮስ ትእዛዝ አስተላለፈ። በባቢሎን መዛግብት ባሉበት ቤተ መጻሕፍት ምርመራ ተደረገ። በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በቤተ መንግሥት ውስጥ አንድ ጥቅል ተገኘ፥ በውስጡም እንዲህ የሚል ተጽፎ ነበር፤ “ማስታወሻ በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ በኢየሩሳሌም ስላለው ስለ እግዚአብሔር ቤት እንዲህ ብሎ አዘዘ፥ መሥዋዕት የሚሠዋበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፥ በጽኑም ይመሥረት፤ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ ስፋቱም ስድሳ ክንድ ይሁን። በሦስት መደዳ ታላላቅ ድንጋይ፥ አንድ መደዳ እንጨት ይደረግ፤ ወጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ። ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች ይመለስ፥ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፥ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር።” “አሁንም በወንዝ ማዶ ያለውን አካባቢ ገዢ የሆንህ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻቸው ባለ ሥልጣናት ከዚያ ራቁ፤ ይህም የእግዚአብሔር ቤት እንዲሠራ ተዉ፥ የአይሁድ አለቃና የአይሁድም ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው እንዲሠሩ ተዉአቸው። ይህን የእግዚአብሔርን ቤት እንዲሠሩ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን አዝዣለሁ፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት ይሰጣቸው፥ ሥራም እንዳታስፈቱአቸው። ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖችና አውራ በጎች ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው። ይህም ለሰማያት አምላክ መልካም መዓዛ እንዲያቀርቡ፥ ለንጉሥና ለልጆቹ ሕይወትም እንዲጸልዩ ነው። ይህንም ትእዛዝ የሚያደናቅፍ ሁሉ፥ ምሰሶ ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰካበት፥ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይሁን ብዬ አዝዣለሁ። ይህን ሊለውጡ፥ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ሊያፈርሱ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙን በዚያ ያኖረው አምላክ ያጥፋው። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፥ በትጋት ይፈጸም።” ከዚያ በኋላ በወንዝ ማዶ ያለ አካባቢ ገዢ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይና ተባባሪዎቻቸው ንጉሡ ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ ሐጌና በዒዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተበረታቱ ሠሩ ተከናወነላቸውም። በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ቂሮስ ትእዛዝ እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስ የፋርስ ንጉሥ ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ።