ዕዝራ 1:1-10

ዕዝራ 1:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በኤ​ር​ም​ያስ አፍ የተ​ና​ገ​ረው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ከተ​ፈ​ጸመ በኋላ በፋ​ርስ ንጉሥ በቂ​ሮስ በመ​ጀ​መ​ሪ​ያው ዓመት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የፋ​ር​ስን ንጉሥ የቂ​ሮ​ስን መን​ፈስ አስ​ነሣ፤ እር​ሱም በመ​ን​ግ​ሥቱ ሁሉ አዋጅ አስ​ነ​ገረ፤ ደግ​ሞም በጽ​ሕ​ፈት እን​ዲህ አለ፦ “የፋ​ርስ ንጉሥ ቂሮስ እን​ዲህ ይላል፦ የሰ​ማይ አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የም​ድ​ርን መን​ግ​ሥ​ታት ሁሉ ሰጥ​ቶ​ኛል፤ በይ​ሁ​ዳም ባለ​ችው በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ቤትን እሠ​ራ​ለት ዘንድ እን​ዳ​ስብ አደ​ረ​ገኝ፤ ከሕ​ዝቡ ሁሉ በእ​ና​ንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አም​ላኩ ከእ​ርሱ ጋር ይሁን፤ እር​ሱም በይ​ሁዳ ወዳ​ለ​ችው ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ይውጣ፤ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ለሚ​ኖ​ረው አም​ላክ፥ ለእ​ስ​ራ​ኤል አም​ላክ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤትን ይሥራ፤ በስ​ደት በሚ​ኖ​ር​ባ​ቸው ከተ​ሞች ሁሉ ለቀ​ረው ሰው ሁሉ የሀ​ገሩ ሰዎች በብ​ርና በወ​ርቅ፥ በዕ​ቃም፥ በእ​ን​ስ​ሳም ይር​ዱት፤ ይህም በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ላለው ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት በፈ​ቃ​ዳ​ቸው ከሚ​ያ​ቀ​ር​ቡት ሌላ ይሁን።” የይ​ሁ​ዳና የብ​ን​ያም የአ​ባ​ቶች ቤቶች አለ​ቆ​ችም፥ ካህ​ና​ቱም፥ ሌዋ​ው​ያ​ኑም፥ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ያለ​ውን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቤት ለመ​ሥ​ራት ይወጡ ዘንድ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ፈ​ሳ​ቸ​ውን ያነ​ሣ​ሣው ሁሉ ተነሡ። በዙ​ሪ​ያ​ቸ​ውም ያሉ ሁሉ በፈ​ቃ​ዳ​ቸው ካቀ​ረ​ቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና በወ​ርቅ፥ በገ​ን​ዘ​ቦ​ችና በእ​ን​ስ​ሶች፥ በሌ​ላም ስጦታ ይረ​ዷ​ቸው ነበር። ንጉሡ ቂሮ​ስም ናቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ወስዶ በአ​ም​ላኩ ቤት ያኖ​ራ​ቸ​ውን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቤተ መቅ​ደስ ዕቃ​ዎች አወጣ። የፋ​ርስ ንጉሥ ቂሮ​ስም የመ​ዝ​ገብ ሐላፊ በነ​በ​ረው በሚ​ት​ሪ​ዳጡ እጅ አወ​ጣ​ቸው፤ ለይ​ሁ​ዳም መስ​ፍን ለሲ​ሳ​ብ​ሳር ቈጠ​ራ​ቸው። ቍጥ​ራ​ቸ​ውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወ​ርቅ ሳሕ​ኖች፥ አንድ ሺህም የብር ሳሕ​ኖች፥ ሃያ ዘጠ​ኝም ቢላ​ዋ​ዎች፥ ሠላሳ የወ​ርቅ ዳካ​ዎች፥ አራት መቶ ዐሥ​ርም ሌላ ዓይ​ነት የብር ዳካ​ዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ።

ዕዝራ 1:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያ ዓመት፣ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንድሠራለት አዝዞኛል። ከሕዝቡ መካከል በእናንተ ዘንድ የሚገኝ ማንኛውም ሰው አምላኩ ከርሱ ጋራ ይሁን፤ በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና በዚያ ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይሥራ። ባሉበት ስፍራ የሚቀሩ በየትኛውም አገር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስጦታ እንዲሆን ከበጎ ፈቃድ ስጦታ በተጨማሪ ብርና ወርቅ፣ ዕቃና እንስሳ በመስጠት ይርዷቸው።’ ” ከዚያም እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው የይሁዳና የብንያም ቤተ ሰብ አለቆች እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ተዘጋጁ። ጎረቤቶቻቸውም ሁሉ በበጎ ፈቃድ ከሰጡት መባ በተጨማሪ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎችን፣ ቍሳቍስን፣ እንስሳትንና ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ስጦታዎችንም በመለገስ ረዷቸው። ከዚህም በላይ ንጉሡ ቂሮስ፣ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤተ ጣዖት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት አወጣ። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በግምጃ ቤቱ ኀላፊ በሚትሪዳጡ አማካይነት ንዋያተ ቅድሳቱ እንዲመጡና በይሁዳው ገዥ በሰሳብሳር ፊት እንዲቈጠሩ አደረገ። የዕቃው ዝርዝር ይህ ነበር፤ የወርቅ ሳሕን 30 የብር ሳሕን 1,000 ዝርግ የብር ሳሕን 29 ጐድጓዳ የወርቅ ሳሕን 30 ባለግጣም የብር ጐድጓዳ ሳሕን 410 ሌሎች ቍሳቍስ 1,000

ዕዝራ 1:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፤ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤ በሚኖርበትም ስፍራ ሁሉ ለቀረው ሰው የአገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን።’” የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ እና በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ። በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና፥ በወርቅ፥ በቍሳቍሶችና በእንስሶች በሌላም ስጦታ አገዙአቸው። ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች አወጣ። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገቡ ላይ በነበረው በሚትሪዳጡ እጅ አወጣቸው፤ ለይሁዳም መስፍን ለሰሳብሳር ቈጠራቸው። ቍጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ፥ አንድ ሺህ የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝ ቢላዎች፥ ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ አሥር ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ።

ዕዝራ 1:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አማካይነት አስቀድሞ የተናገረውን የትንቢት ቃል የፋርስ ተወላጅ ቂሮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ፈጸመው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ራሱ ቂሮስን አነሣሥቶ ከዚህ የሚከተለውን ትእዛዝ በጽሑፍ በማወጅ በንጉሠ ነገሥት ግዛቱ ሁሉ እንዲነበብ አደረገ። የፋርስ ንጉሠ ነገሥትም በዐዋጅ የሰጠው ትእዛዝ እንዲህ የሚል ነበር፦ “የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የዓለም ሁሉ ገዢ አድርጎኛል፤ እርሱም ቤተ መቅደስን በይሁዳ ምድር በምትገኘው በኢየሩሳሌም እንድሠራለት አዞኛል። ከእናንተ መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆነ ሁሉ፥ አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደሚገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይሥራ። እነዚህ ከሞት የተረፉት ሰዎች በሚመለሱበት ጊዜ በአካባቢአቸው የሚኖሩ ሰዎች ብርና ወርቅ፥ ዕቃና የጭነት ከብቶች ይርዱአቸው፤ ይህም በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው ከሚሰጡት መባ ሌላ ነው።” ከዚያም በኋላ የይሁዳና የብንያም ነገዶች የቤተሰብ አለቆች፥ ካህናትና ሌዋውያን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ልቡን ያነሣሣው ሌላውም ሰው ሁሉ፥ ተመልሶ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደገና ለመሥራት ተዘጋጀ። ጐረቤቶቻቸውም ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎችን፥ ቈሳቊሶችንና ከብቶችን፥ ሌሎችንም ጠቃሚ የሆኑ ስጦታዎችና በቤተ መቅደስ መባ ሆኖ የሚቀርብ ሌላም ነገር በመለገሥ ረዱአቸው። ከዚህም በቀር ቂሮስ ቀድሞ ንጉሥ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ዘርፎ በመውሰድ በአማልክቱ ቤተ መቅደስ ያኖራቸውን እንደ ጽዋ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት መልሶ ሰጣቸው። የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ እነዚያን ንዋያተ ቅድሳት ሚትረዳት ተብሎ በሚጠራው በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ አስቈጥሮ የይሁዳ ገዢ ለሆነው ለሼሽባጻር አስረከበው፤ የዕቃውም ዝርዝር እንደሚከተለው ነበር፦ ለመባ መሰብሰቢያ የሚሆኑ ከወርቅ የተሠሩ ሳሕኖች 30 ለመባ መሰብሰቢያ የሚሆኑ ከብር የተሠሩ ሳሕኖች 1000 ሌሎች ልዩ ልዩ ሳሕኖች 29 ከወርቅ የተሠሩ ወጭቶች 30 ከብር የተሠሩ ወጭቶች 410 ሌሎች ልዩ ልዩ ዕቃዎች 1000

ዕዝራ 1:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት፥ በኤርምያስ አፍ የተናገረው የጌታ ቃል እንዲፈጸም፥ ጌታ የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፥ ይህም በመንግሥቱ ሁሉ በአዋጅና በጽሑፍ እንዲያስነግር ነው፤ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ “የሰማያት አምላክ ጌታ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፥ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እንድሠራለት አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ ማንም በእናንተ ውስጥ የሚኖር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ የጌታ የእስራኤል አምላክን ቤት ይሥራ፥ እርሱም በኢየሩሳሌም ያለ አምላክ ነው፤ ከሁሉም ስፍራዎች የተረፈው ሁሉ መፃተኛ ሆኖ በሚኖርበት የሰፈሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፥ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት መባ ጋር ይሁን።” እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው የይሁዳና የብንያም የአባቶች አለቆች፥ ካህናቱና ሌዋውያኑም ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም ያለውን የጌታን ቤት ለመሥራት ተዘጋጁ። በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት መባ ሁሉ በተጨማሪ በእጃቸው፥ በብር ዕቃና በወርቅ፥ በዕቃዎችና በእንስሶችና በውድ ነገሮች አበረታቱአቸው። ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የጌታን ቤት ዕቃዎች አወጣ። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገብ ቤቱ በሚትረዳት እጅ አወጣቸው፥ ለይሁዳም መስፍን ለሼሽባጻር ቆጠራቸው። ቁጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ ሰሐኖች፥ አንድ ሺህ የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝ ቢላዋዎች፥ ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ ዐሥር ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ።