መጽሐፈ ዕዝራ 1:1-10

መጽሐፈ ዕዝራ 1:1-10 አማ05

እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ አማካይነት አስቀድሞ የተናገረውን የትንቢት ቃል የፋርስ ተወላጅ ቂሮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ፈጸመው፤ ይኸውም እግዚአብሔር ራሱ ቂሮስን አነሣሥቶ ከዚህ የሚከተለውን ትእዛዝ በጽሑፍ በማወጅ በንጉሠ ነገሥት ግዛቱ ሁሉ እንዲነበብ አደረገ። የፋርስ ንጉሠ ነገሥትም በዐዋጅ የሰጠው ትእዛዝ እንዲህ የሚል ነበር፦ “የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የዓለም ሁሉ ገዢ አድርጎኛል፤ እርሱም ቤተ መቅደስን በይሁዳ ምድር በምትገኘው በኢየሩሳሌም እንድሠራለት አዞኛል። ከእናንተ መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆነ ሁሉ፥ አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደሚገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይሥራ። እነዚህ ከሞት የተረፉት ሰዎች በሚመለሱበት ጊዜ በአካባቢአቸው የሚኖሩ ሰዎች ብርና ወርቅ፥ ዕቃና የጭነት ከብቶች ይርዱአቸው፤ ይህም በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው ከሚሰጡት መባ ሌላ ነው።” ከዚያም በኋላ የይሁዳና የብንያም ነገዶች የቤተሰብ አለቆች፥ ካህናትና ሌዋውያን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ልቡን ያነሣሣው ሌላውም ሰው ሁሉ፥ ተመልሶ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደገና ለመሥራት ተዘጋጀ። ጐረቤቶቻቸውም ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎችን፥ ቈሳቊሶችንና ከብቶችን፥ ሌሎችንም ጠቃሚ የሆኑ ስጦታዎችና በቤተ መቅደስ መባ ሆኖ የሚቀርብ ሌላም ነገር በመለገሥ ረዱአቸው። ከዚህም በቀር ቂሮስ ቀድሞ ንጉሥ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ዘርፎ በመውሰድ በአማልክቱ ቤተ መቅደስ ያኖራቸውን እንደ ጽዋ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት መልሶ ሰጣቸው። የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ እነዚያን ንዋያተ ቅድሳት ሚትረዳት ተብሎ በሚጠራው በቤተ መንግሥቱ ዕቃ ግምጃ ቤት ኀላፊ አስቈጥሮ የይሁዳ ገዢ ለሆነው ለሼሽባጻር አስረከበው፤ የዕቃውም ዝርዝር እንደሚከተለው ነበር፦ ለመባ መሰብሰቢያ የሚሆኑ ከወርቅ የተሠሩ ሳሕኖች 30 ለመባ መሰብሰቢያ የሚሆኑ ከብር የተሠሩ ሳሕኖች 1000 ሌሎች ልዩ ልዩ ሳሕኖች 29 ከወርቅ የተሠሩ ወጭቶች 30 ከብር የተሠሩ ወጭቶች 410 ሌሎች ልዩ ልዩ ዕቃዎች 1000