መጽሐፈ ዕዝራ 1:1-10

መጽሐፈ ዕዝራ 1:1-10 አማ54

በኤርምያስም አፍ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፤ ደግሞም በጽሕፈት አድርጎ እንዲህ አለ “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፤ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖረው አምላክ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሥራ፤ በሚኖርበትም ስፍራ ሁሉ ለቀረው ሰው የአገሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፤ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት ሌላ ይሁን።’” የይሁዳና የብንያም የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ እና በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው ሁሉ ተነሡ። በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት ሁሉ ሌላ በብር ዕቃና፥ በወርቅ፥ በቍሳቍሶችና በእንስሶች በሌላም ስጦታ አገዙአቸው። ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች አወጣ። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገቡ ላይ በነበረው በሚትሪዳጡ እጅ አወጣቸው፤ ለይሁዳም መስፍን ለሰሳብሳር ቈጠራቸው። ቍጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ፥ አንድ ሺህ የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝ ቢላዎች፥ ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ አሥር ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ።