ዕዝራ 1:1-10

ዕዝራ 1:1-10 NASV

በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያ ዓመት፣ በኤርምያስ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በግዛቱ ሁሉ ዐዋጅ እንዲያስነግርና ይህም እንዲጻፍ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፤ “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንድሠራለት አዝዞኛል። ከሕዝቡ መካከል በእናንተ ዘንድ የሚገኝ ማንኛውም ሰው አምላኩ ከርሱ ጋራ ይሁን፤ በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣና በዚያ ለሚኖረው አምላክ፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ይሥራ። ባሉበት ስፍራ የሚቀሩ በየትኛውም አገር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስጦታ እንዲሆን ከበጎ ፈቃድ ስጦታ በተጨማሪ ብርና ወርቅ፣ ዕቃና እንስሳ በመስጠት ይርዷቸው።’ ” ከዚያም እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው የይሁዳና የብንያም ቤተ ሰብ አለቆች እንዲሁም ካህናቱና ሌዋውያኑ ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት ተዘጋጁ። ጎረቤቶቻቸውም ሁሉ በበጎ ፈቃድ ከሰጡት መባ በተጨማሪ ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎችን፣ ቍሳቍስን፣ እንስሳትንና ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ስጦታዎችንም በመለገስ ረዷቸው። ከዚህም በላይ ንጉሡ ቂሮስ፣ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤተ ጣዖት ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንዋያተ ቅድሳት አወጣ። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በግምጃ ቤቱ ኀላፊ በሚትሪዳጡ አማካይነት ንዋያተ ቅድሳቱ እንዲመጡና በይሁዳው ገዥ በሰሳብሳር ፊት እንዲቈጠሩ አደረገ። የዕቃው ዝርዝር ይህ ነበር፤ የወርቅ ሳሕን 30 የብር ሳሕን 1,000 ዝርግ የብር ሳሕን 29 ጐድጓዳ የወርቅ ሳሕን 30 ባለግጣም የብር ጐድጓዳ ሳሕን 410 ሌሎች ቍሳቍስ 1,000