መጽሐፈ ዕዝራ 1:1-10

መጽሐፈ ዕዝራ 1:1-10 መቅካእኤ

በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት፥ በኤርምያስ አፍ የተናገረው የጌታ ቃል እንዲፈጸም፥ ጌታ የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፥ ይህም በመንግሥቱ ሁሉ በአዋጅና በጽሑፍ እንዲያስነግር ነው፤ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ “የሰማያት አምላክ ጌታ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፥ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እንድሠራለት አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ ማንም በእናንተ ውስጥ የሚኖር አምላኩ ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም በይሁዳ ወዳለችው ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፥ የጌታ የእስራኤል አምላክን ቤት ይሥራ፥ እርሱም በኢየሩሳሌም ያለ አምላክ ነው፤ ከሁሉም ስፍራዎች የተረፈው ሁሉ መፃተኛ ሆኖ በሚኖርበት የሰፈሩ ሰዎች በብርና በወርቅ በዕቃም በእንስሳም ይርዱት፥ ይህም በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር ቤት በፈቃዳቸው ከሚያቀርቡት መባ ጋር ይሁን።” እግዚአብሔር መንፈሳቸውን ያነሣሣው የይሁዳና የብንያም የአባቶች አለቆች፥ ካህናቱና ሌዋውያኑም ሁሉ ለመሄድና በኢየሩሳሌም ያለውን የጌታን ቤት ለመሥራት ተዘጋጁ። በዙሪያቸውም ያሉ ሁሉ በፈቃዳቸው ካቀረቡት መባ ሁሉ በተጨማሪ በእጃቸው፥ በብር ዕቃና በወርቅ፥ በዕቃዎችና በእንስሶችና በውድ ነገሮች አበረታቱአቸው። ንጉሡ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በአማልክቱ ቤት ያኖራቸውን የጌታን ቤት ዕቃዎች አወጣ። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም በመዝገብ ቤቱ በሚትረዳት እጅ አወጣቸው፥ ለይሁዳም መስፍን ለሼሽባጻር ቆጠራቸው። ቁጥራቸውም ይህ ነው፤ ሠላሳ የወርቅ ሰሐኖች፥ አንድ ሺህ የብር ሰሐኖች፥ ሀያ ዘጠኝ ቢላዋዎች፥ ሠላሳ የወርቅ ደካዎች፥ አራት መቶ ዐሥር ሌላ ዓይነት የብር ደካዎች፥ አንድ ሺህም ሌላ ዕቃ ነበረ።