ሕዝቅኤል 3:1-15

ሕዝቅኤል 3:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እር​ሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ያገ​ኘ​ኸ​ውን ብላ፤ ይህን መጽ​ሐፍ ብላ፤ ሄደ​ህም ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች ተና​ገር” አለኝ። አፌ​ንም ከፈ​ትሁ፤ መጽ​ሐ​ፉ​ንም አበ​ላኝ። እር​ሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! አፍህ ይብላ፤ በም​ሰ​ጥ​ህም በዚህ መጽ​ሐፍ ሆድ​ህን ሙላ” አለኝ። እኔም በላ​ሁት፤ በአ​ፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ። እን​ዲ​ህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ተነ​ሥ​ተህ ወደ እስ​ራ​ኤል ቤት ሂድና ግባ፥ ቃሌ​ንም ንገ​ራ​ቸው። ወደ እስ​ራ​ኤል ቤት እንጂ ንግ​ግ​ራ​ቸው ልዩ ወደ ሆነ፥ ቋን​ቋ​ቸ​ውም ወደ​ማ​ይ​ታ​ወቅ ሕዝብ አል​ተ​ላ​ክ​ህ​ምና፤ ንግ​ግ​ራ​ቸው ልዩ ወደ ሆነ፥ ቋን​ቋ​ቸ​ውም ሌላ ወደ ሆነ፥ ቃላ​ቸ​ው​ንም ታውቅ ዘንድ ወደ​ማ​ይ​ቻ​ልህ ሕዝብ አል​ላ​ክ​ሁ​ህም። ወደ እነ​ዚ​ያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰ​ሙህ ነበር። ነገር ግን የእ​ስ​ራ​ኤል ቤት ሁሉ ክፉ​ዎ​ችና ልበ ደን​ዳ​ኖች ናቸ​ውና፥ እኔ​ንም መስ​ማት እንቢ ብለ​ዋ​ልና የእ​ስ​ራ​ኤል ቤት አን​ተን አይ​ሰ​ሙ​ህም። እነሆ ፊት​ህን በፊ​ታ​ቸው አጸ​ና​ሁት፤ ኀይ​ል​ህ​ንም ከኀ​ይ​ላ​ቸው ይልቅ አጸ​ና​ለሁ። ሁል​ጊዜ ከዓ​ለት ይልቅ ትጸ​ና​ለህ፤ አት​ፍ​ራ​ቸው፤ ከፊ​ታ​ቸ​ውም አት​ደ​ን​ግጥ፤ ዐመ​ፀኛ ቤት ናቸ​ውና።” እር​ሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! የነ​ገ​ር​ሁ​ህን ቃሌን ሁሉ በል​ብህ ጠብ​ቀው፤ በጆ​ሮ​ህም ስማው። ተነ​ሥ​ተ​ህም ወደ ተማ​ረኩ ወደ ወገ​ንህ ልጆች ሂድ፤ እነ​ር​ሱም ቢሰሙ ወይም ቢፈሩ፦ ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል ብለህ ንገ​ራ​ቸው” አለኝ። መን​ፈ​ስም ወደ ላይ ወሰ​ደኝ፤ በኋ​ላ​ዬም፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ክብር ከቦ​ታው ይባ​ረክ” የሚል የታ​ላቅ ንው​ጽ​ው​ጽታ ድምፅ ሰማሁ። የእ​ነ​ዚ​ያም እን​ስሳ ክን​ፎች እርስ በር​ሳ​ቸው ሲማቱ፥ በአ​ጠ​ገ​ባ​ቸ​ውም የመ​ን​ኰ​ራ​ኵ​ሮ​ችን ድምፅ፥ የታ​ላ​ቁ​ንም ንው​ጽ​ው​ጽታ ድምፅ ሰማሁ። መን​ፈ​ስም አን​ሥቶ ወሰ​ደኝ፤ እኔም በም​ሬ​ትና በመ​ን​ፈሴ ሙቀት ሄድሁ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እጅ በላዬ በር​ትታ ነበር። በቴ​ል​አ​ቢ​ብም ወደ አሉ፥ በኮ​ቦ​ርም ወንዝ አጠ​ገብ ወደ ተቀ​መጡ ምር​ኮ​ኞች መጣሁ፤ በተ​ቀ​መ​ጡ​በ​ትም ቦታ ተቀ​መ​ጥሁ፤ በዚ​ያም በመ​ካ​ከ​ላ​ቸው እየ​ተ​መ​ላ​ለ​ስሁ ሰባት ቀን ተቀ​መ​ጥሁ።

ሕዝቅኤል 3:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በፊትህ ያለውን ብላ፤ ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላና ሄደህ ለእስራኤል ቤት ተናገር” አለኝ። ስለዚህ አፌን ከፈትሁ፤ እርሱም መጽሐፉን አጐረሠኝ። እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምሰጥህን ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላ፤ ሆድህንም ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠኝ። እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፤ ቃሌንም ንገራቸው። ወደ እስራኤል ቤት እንጂ፣ ንግግሩ ወደማይገባና ቋንቋው ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህም፤ ንግግራቸው ወደማይገባና ቋንቋቸው ወደማይታወቅ፣ ቃላቸውንም መረዳት ወደማይቻልህ ብዙ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥ ይሰሙህ ነበር። ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለ ሆኑ ሊሰሙኝ አልፈለጉም፤ ስለዚህ የእስራኤል ቤት አንተንም አይሰሙህም። እነሆ እኔ በእነርሱ ፊት የማትበገር ጠንካራ አደርግሃለሁ። ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር አልማዝ አደርገዋለሁ። ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም እንኳ አትፍራቸው፤ በፊታቸውም አትሸበር።” እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የምነግርህን ቃል ሁሉ በጥንቃቄ አድምጥ፤ በልብህም ያዝ። ተነሥተህም በምርኮ ወዳሉት ወገኖችህ ሄደህ ተናገራቸው፤ ቢሰሙህም ባይሰሙህም፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ በላቸው።” መንፈስም ወደ ላይ ከፍ አድርጎ አነሣኝ፤ ከኋላዬም፣ “የእግዚአብሔር ክብር በማደሪያ ስፍራው ይባረክ!” የሚል ታላቅ ህምህምታ ሰማሁ፤ ይህም የሕያዋኑ ፍጡራን ክንፎች እርስ በርስ ሲጋጩና በአጠገባቸው ያሉት መንኰራኵሮች የሚያሰሙት ታላቅ ህምህምታ ነበር። መንፈስ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ወሰደኝ፤ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ቍጣ ሄድሁ፤ የእግዚአብሔርም ጽኑ እጅ በላዬ ነበረች። ከዚያም በኮቦር ወንዝ አጠገብ በቴልአቢብ ወደሚኖሩት ምርኮኞች መጣሁ፣ በድንጋጤ ፈዝዤም ከእነርሱ ጋራ ሰባት ቀን በመካከላቸው ተቀመጥሁ።

ሕዝቅኤል 3:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ያገኘኸውን ብላ፥ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ። አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ። እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ። እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ተናገራቸው። ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህምና፥ ንግግራቸው ወደ ጠለቀው ቋንቋቸውም ወደማይታወቅ ቃላቸውንም ታውቅ ዘንድ ወደማይቻልህ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነዚያስ ልኬህ ቢሆን ኖሮ በሰሙህ ነበር። ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና፥ እኔንም መስማት እንቢ ብለዋልና የእስራኤል ቤት አንተን አይሰሙም። እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ። ከቡላድ ድንጋይ ይልቅ እንዳለ አልማዝ ግምባርህን አጠንክሬአለሁ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ቢሆኑ አትፍራቸው፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ። እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የነገርሁህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ተቀበል በጆሮህም ስማ። ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፥ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው አለኝ። መንፈስም አነሣኝ፥ በኋላዬም፦ የእግዚአብሔር ክብር ከቦታው ይባረክ የሚል የጽኑ ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ። የአራቱም እንስሳ ክንፎች እርስ በርሳቸው ሲማቱ፥ በአጠገባቸውም የመንኰራኵሮችን ድምፅ፥ የጽኑውንም ንውጥውጥታ ድምፅ ሰማሁ። መንፈስ አንሥቶ አስወገደኝ፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ሙቀት ሄድሁ፥ የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ በርትታ ነበር። በቴልአቢብም ወዳሉ በኮቦርም ወንዝ አጠገብ ወደ ተቀመጡ ምርኮኞች መጣሁ፥ በተቀመጡበትም ቦታ ተቀመጥሁ፥ በዚያም ሰባት ቀን በድንጋጤ በመካከላቸው ተቀመጥሁ።

ሕዝቅኤል 3:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔርም “የሰው ልጅ ሆይ! የቀረበልህን ብላ፥ ይህን የብራና ጥቅል ብላ፤ ወደ እስራኤልም ሕዝብ ሄደህ ተናገር!” አለኝ። ስለዚህ አፌን ከፈትኩ፤ የብራናውንም ጥቅል እንድበላው ሰጠኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን የሰጠሁህን የብራና ጥቅል ብላው! ሆድህንም በእርሱ ሙላው!” አለኝ፤ እኔም በበላሁት ጊዜ ጣፋጭነቱ እንደ ማር. ነበር። ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄደህ እኔ የምነግርህን ቃል ንገራቸው፤ እኔ የምልክህ ወደ እስራኤላውያን እንጂ ቋንቋቸው ወደማይታወቅ ባዕዳን ሕዝብ አይደለም፤ ንግግራቸው ግራ የሚያጋባ፥ ቋንቋቸው ወደማይታወቅና የቃላቸውን ትርጒም ልታስተውለው ወደማትችል ታላላቅ ሕዝቦች ልኬህ ቢሆን ኖሮማ በሰሙህ ነበር። ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለ ሆኑ እኔን ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ አንተንም አይሰሙህም። እኔ ግን አንተን እንደ እነርሱ እልኸኛና የማትበገር አደርግሃለሁ። አንዳችም የሚገታህ ነገር እስከማይኖር ድረስ መልእክቴን ለመናገር ቈራጥ ትሆናለህ፤ አንተን ይበልጥ ያጠነከርኩህ ስለ ሆነ እነዚህን በዕብሪት ዐመፀኞች የሆኑትን የምትፈራበት ምንም ምክንያት የለም።” ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የምናገረውን ሁሉ በጥንቃቄ አድምጠህ አስብበት። በምርኮ ወደሚገኙት የአገርህ ሕዝብ ሄደህ ቢሰሙህም ባይሰሙህም እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ሁሉ ንገራቸው።” ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ላይ ከፍ አደረገኝ፤ ከበስተኋላዬም “በሰማይ ለሚኖር እግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ይሁን!” የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ። የሕያዋን ፍጥረቶቹ ክንፎቹ እርስ በርሳቸው በአየር ላይ ሲፋጩ ሰማሁ፤ ከመንኰራኲሮቹም የሚሰማው የጋጋታ ድምፅ ከፍተኛ ነበር። መንፈስ አንሥቶ በወሰደኝ ጊዜ ስሜቴ በምሬትና በቊጣ ተሞልቶ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ኀይል በእኔ ላይ በርትቶ ነበር። ስለዚህ በኬባር ወንዝ አጠገብ ወዳለው ወደ ቴል አቢብ መጣሁ፤ ይህም ስፍራ የምርኮኞች መኖሪያ ነበር፤ ባየሁትና በሰማሁት ነገር ሁሉ በመደንገጥ ደንዝዤ በመካከላቸው ሰባት ቀን ቈየሁ።

ሕዝቅኤል 3:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እርሱም እንንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የቀረበልኽን ብላ፥ ይህን መጽሐፍ ብላ፥ ሄደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር። አፌንም ከፈትሁ መጽሐፉንም አጐረሰኝ። እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አፍህ ይብላ፥ በምሰጥህም በዚህ መጽሐፍ ሆድህን ሙላ አለኝ። እኔም በላሁት፥ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠ። እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፥ ቃሌንም ንገራቸው። ወደ እስራኤል ቤት እንጂ ንግግራቸው ወደ ጠለቀ፥ ቋንቋቸውም ከባድ ወደ ሆነ ሕዝብ አልተላክህምና፥ ንግግራቸው ጥልቅ ወደ ሆነ፥ ቋንቋቸውም ከባድ ወደ ሆነ፥ ቃላቸውንም መስማት ወደማይቻልህ ታላላቅ ሕዝቦች አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ ይሰሙህ ነበር። ነገር ግን የእስራኤል ቤት እኔን መስማት እንቢ ብለዋልና አንተንም አይሰሙህም፥ ምክንያቱም የእስራኤል ቤት ሁሉ የጠነከረ ግምባርና የደነደነ ልብ አላቸውና። እነሆ፥ ፊትህን በፊታቸው ግምባርህንም በግምባራቸው አጠንክሬአለሁ። ግምባርህን ከባልጩት እንደሚጠነክር አልማዝ አድርጌዋለሁ፥ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና አትፍራቸው፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ። እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ቃሌን ሁሉ በልብህ ያዝ፥ በጆሮህም ስማ። ተነሥተህም ወደ ተማረኩት፥ ወደ ሕዝብህ ልጆች ሂድ፥ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው። መንፈስም አነሣኝ፥ ከኋላዬም የጌታ ክብር ከሥፍራው ይባረክ የሚል ታላቅ የሚያጉረመርም ድምፅ ሰማሁ። ይህም የሕያዋኑ ክንፎች እርስ በእርሳቸው ሲማቱ የሚወጣው ድምፅ፥ በአጠገባቸውም የነበሩት የመንኰራኵሮች ድምፅ ነበር፥ እርሱም ታላቅ የሚያጉረመርም ድምፅ ነበር። መንፈስ አነሳኝ፥ ወሰደኝም፥ እኔም በምሬትና በመንፈሴ ቁጣ ሄድሁ፥ የጌታም እጅ በላዬ ላይ በርትታ ነበር። በኮቦር ወንዝ አጠገብ ወደሚኖሩ፥ በቴልአቢብም ወዳሉ ምርኮኞች መጣሁ፥ በዚያ በሚኖሩበትም ሰባት ቀን በመካከላቸው በድንጋጤ ተቀመጥሁ።